በአማራ ክልል ሰላምን በዘላቂነት  ለማስፈን  የሃይማኖት አባቶች ድጋፋቸውን አጠናክረው እንዲቀጥሉ ተጠየቀ

ጎንደር፤ ሰኔ 4/2016(ኢዜአ)፡-  በአማራ ክልል ሰላምን በዘላቂነት ለማስፈን  በሚደረገው ጥረት  የሃይማኖት አባቶች ድጋፋቸውን  አጠናክረው እንዲቀጥሉ ተጠየቀ። 

በጎንደር ከተማ የሚገኙ የሃይማኖት አባቶች በሰላምና ሌሎች ወቅታዊ ጉዳዮች ዙሪያ ከክልሉና ከከተማ አስተዳደሩ ከፍተኛ አመራር አባላት ጋር  ዛሬ ተወያይተዋል። 

በምክትል ርእሰ መስተዳድር ማዕረግ የአስተዳደር ጉዳዮች ክላስተር አስተባባሪና የአማራ ክልል ሰላምና ጸጥታ ቢሮ ሃላፊ አቶ ደሳለኝ ጣሰው በውይይቱ ላይ እንደገለጹት፤በክልሉ አስተማማኝ ሰላም ለማረጋገጥ በተደረገው ጥረት የሃይማኖት አባቶች ላበረከቱት አስተዋጽኦ የክልሉ መንግስት እውቅና የሚሰጠው ጉዳይ ነው፡፡

በተለይም የክልሉ መንግስት ያቀረበውን የሰላም ጥሪ ተከትሎ ችግር ውስጥ ገብተው የነበሩ ወገኖች እንዲመለሱ በማድረግ የሃይማኖት መሪዎች ያበረከቱት አስተዋጽኦ በታሪክ የሚታወስ መሆኑን አስታውቀዋል።

በዚህም በክልሉ ከ12ሺ 800 በላይ ታጣቂዎች ሰላማዊ አማራጭን በመከተል የተሃድሶ ስልጠና ወስደው ከማህበረሰቡ ጋር በመቀላቀል ሰላማዊ ህይወት በመምራት ላይ እንደሚገኙ ተናግረዋል፡፡

አሁን ላይ በክልሉ የተገኘውን ሰላም አጽንቶ ለማስቀጠል በሚደረገው ጥረት የሃይማኖት አባቶች በሃይማኖታዊ አስተምህሮ ለሰላም እሴቶች ግንባታ አበክረው እንዲሰሩ ጠይቀዋል፡፡

በዚህም ድጋፋቸውን አጠናክረው እንዲቀጥሉ ጥሪ አቅርበዋል፡፡

የከተማውን ሰላም በዘላቂነት ለማስቀጠል በተከናወኑ ስራዎች ውስጥ የሃይማኖት አባቶችና መሪዎች አስተዋጽኦ ከፍተኛ  እንደነበር  የገለጹት ደግሞ የጎንደር ከተማ አስተዳደር ተቀዳሚ ምክትል ከንቲባ አቶ ባዩህ አቡሃይ ናቸው፡፡ 


 

በሃይማኖት አባቶችና በህብረተሰቡ እገዛ በከተማው በሰፈነው ሰላም በርካታ ነባር የልማት ፕሮጀክቶችን ማስቀጠልና አዳዲስ ፕሮጀክቶችን ማስጀመር መቻሉን አስረድተዋል።

የውይይቱ ተሳታፊ የሃይማኖት አባቶች፤ ለምዕመናን በሚሰጡት ትምህርት ስለ ሰላም አስፈላጊነትና ጠቀሜታ አጥብቀው መስበካቸውን እንደሚቀጥሉ ተናግረዋል፡፡ 

በውይይት መድረኩ የክልሉና የከተማ አስተዳደሩ ከፍተኛ አመራር አባላት፣ ከከተማው ቤተ እምነቶች  የተውጣጡ የሃይማኖት አባቶችና መሪዎች ተሳታፊ ሆነዋል፡፡ 

 

 

 

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም