መከላከያ ሰራዊት የትኛውንም ግዳጅ በላቀ ብቃትና ጀግንነት መወጣት የሚያስችል ዝግጁነት አለው

አዲስ አበባ፤ ሰኔ 4/2016(ኢዜአ)፦ መከላከያ ሰራዊት በሀገር ውስጥም ሆነ በውጭ የሰላም ማስከበር ተልእኮ በላቀ ብቃትና ጀግንነት ግዳጁን መወጣት የሚያስችል ዝግጁነት ያለው መሆኑን በመከላከያ ህብረት ዘመቻ ዋና መምሪያ የኃይል ሥምሪትና ክትትል መምሪያ ኃላፊ ሜጀር ጀነራል ተስፋዬ አያሌው ገለጹ፡፡

"የጀግንነት ሥነ ልቦና" መጽሐፍ እና ሌሎች የሰራዊቱ ሰነዶች የኢትዮጵያን ሉዓላዊነትና የግዛት አንድነት ለማስከበር ሁሉም ዜጋ የአዕምሮ ዝግጁነት እንዲኖረው የሚያግዙ መሆናቸውንም ገልጸዋል፡፡ 

በመከላከያ ህብረት ዘመቻ ዋና መመሪያ የኃይል ሥምሪትና ክትትል መምሪያ ኃላፊ ሜጀር ጀነራል ተስፋዬ አያሌው እንደተናገሩት፤ በኢትዮጵያ የዘር ፖለቲካ መከባበርን፣ መደጋገፍን የዘነጋ የአንድነት ጸር ሆኖ በመቆየቱ የለውጡ መንግስት በመከላከያ ሰራዊት ላይ ባካሔደው ሪፎርም ሁሉንም ያማከለ ህብረ ብሄራዊ ሰራዊት ገንብቷል፡፡

በተጨማሪም እንደ "የጀግንነት ሥነ ልቦና" ባሉ መጽሐፍት ወደ ጸጥታ ተቋማት የሚቀላቀሉ ወጣቶችን ኢትዮጵያዊ የጀግንነትና ሥነ ልቦና በማስታጠቅ አሻራን መሳረፍ ይገባል ብለዋል፡፡ 

መከላከያ ሰራዊት በውስጥም ሆነ በውጭ የሚሰጠውን ግዳጅ በላቀ ብቃትና ጀግንነት መወጣት የሚያስችል ዝግጁነት ያለው መሆኑን አረጋግጠዋል።

የኢትዮጵያ መከላከያ ሰራዊት የሀገር ክብርና ሉአላዊነት መከታ ከመሆኑም ባለፈ በቀጣናው ሰላም ማስከበር ተልእኮ የላቀ ስምና ክብር ያለው መሆኑን ገልጸዋል።

የኢትዮጵያን ጠንካራ ኢኮኖሚ የመገንባት ሂደት አንዳንዶች በስጋት የሚያዩ መኖራቸውን ጠቅሰው ለሀገር ክብርና ሉዓላዊነት መከበር በተለይም ወጣቶች የላቀ ሚናቸውን ሊወጡ ይገባል ብለዋል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም