የ2017 በጀት ዓመት ረቂቅ በጀት ለሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት ቀረበ

አዲስ አበባ፤ ሰኔ 4/2016(ኢዜአ)፦የ2017 በጀት ዓመት ረቂቅ በጀት 971 ነጥብ 2 ቢሊዮን ብር ሆኖ ለሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት ቀርቧል።

ረቂቅ በጀቱ ከ2016 በጀት አንጻር የ21 ነጥብ 1 በመቶ ብልጫ እንዳለው ተጠቁሟል።

የሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት 31ኛ መደበኛ ስብሰባውን እያደረገ ነው።

ምክር ቤቱ በስብሰባው፤  የገንዘብ ሚኒስትር አሕመድ ሽዴ የፌደራል መንግስት የ2017  በጀት ዓመት ረቂቅ በጀት መግለጫ  አዳምጧል።

ሚኒስትሩ በማብራሪያቸው ረቂቅ በጀቱ ከሁለተኛው አገር በቀል ኢኮኖሚ ማሻሻያ ጋር በተጣጣመ መልኩ መዘጋጀቱንና  ጤናማ የፊስካል ስርዓት ማረጋገጥን አላማ ያደረገ መሆኑን አመልክተዋል። 

ረቂቅ በጀቱ የተዘጋጀው ቅድሚያ ትኩረት የሚደረግባቸው የገቢና የወጪ የፊስካል ፖሊሲ አቅጣጫዎችን፣ ወቅታዊ የማክሮ ኢኮኖሚ ሁኔታንና የኢኮኖሚ ማሻሻያውን የትኩረት አቅጣጫ ባገናዘበ መልኩ እንደሆነም ተናግረዋል።

ለዚህም ገቢን በማሳደግና የወጪ ሽግሽጎችን ተግባራዊ በማድረግ የበጀት ጉድለትን ትርጉም ባለው መልኩ መቀንስንም ታሳቢ አድርጓል ነው ያሉት ሚኒስትሩ። 

በዚሁ መሰረት የ2017 ዓ.ም ረቂቅ በጀት 971 ነጥብ 2 ቢሊዮን ብር ሆኖ መቅረቡን ይህም ከተያዘው በጀት ዓመት አንጻር የ21 ነጥብ 1 በመቶ ወይም የ169 ነጥብ 56 ቢሊዮን ብር ብልጫ እንዳለው ገልጸዋል።

ከዚህም ውስጥ 451 ነጥብ 3 ቢሊዮን ብር ለመደበኛ፣  283 ነጥብ 2 ቢሊዮን ለካፒታል ወጪዎች እና 236 ነጥብ 7 ቢሊዮን ለክልል መንግስታት የበጀት ድጋፍ የተመደበ ነው።

ለክልል መንግስታት ከተመደበው የበጀት ድጋፍ 14 ቢሊዮን የሚሆነው ለዘላቂ ልማት ግቦች ማስፈጸሚያ እንደሚውልም አመልክተዋል።

ከተያዘው በጀት  ውስጥ 502 ቢሊዮን ከገቢ ግብር ለመሰብሰብ መታቀዱንና በአጠቃላይ 563 ነጥብ 6 ቢሊዮን ታክስና ታክስ ካልሆኑ ገቢዎች ለማሰባሰብ መታሰቡን ጠቁመዋል።

ከተመደበው በጀት 139 ነጥብ 3 ቢሊዮን ብሩ ለእዳ ክፍያ እንደሚውልም ነው ሚኒስትሩ ያብራሩት።

የበጀት ጉድለቱን ትርጉም ባለው መልኩ መቀነሱን አመልክተዋል።

ባለበጀት መስሪያ ቤቶች የተመደበላቸውን በጀት ለታለመለት አላማ በቁጠባና በላቀ ውጤታማነት ማዋል እንዳለባቸው አሳስበዋል። 

የመንግስት ግዢዎች ሕጋዊ ስርዓትን በተከተለ መልኩ መከናወን እንደሚገባቸውም በመግለጽ።

ምክር ቤቱ በረቂቅ በጀቱ ላይ ከተወያየ ለዝርዝር እይታ ለፕላን፣ በጀትና ፋይናንስ ጉዳዮች ቋሚ ኮሚቴ ይመራል ተብሎ ይጠበቃል።

የሚኒስትሮች ምክር ቤት ባለፈው ሳምንት ባደረገው 34ኛው መደበኛ ስብሰባ የ2017 ዓ.ም የፌደራል መንግስት በጀት ላይ ከተወያየ በኋላ ግብአቶችን በማከል ወደ ህዝብ ተወካዮች ምክር ቤት እንዲተላለፍ በሙሉ ድምጽ መወሰኑ ይታወቃል።

 

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም