በክልሎቹ የእንሰት ልማትን በማስፋፋት የአፈር ለምነትን ለመጠበቅና የምግብ ዋስትናን ለማረጋገጥ ትኩረት ተደርጓል

አዳማ፤ ሰኔ 4/2016(ኢዜአ)፦ በክልሎቹ የእንሰት ልማትን በማስፋፋት የአፈር ለምነት በዘላቂነት ለመጠበቅና የምግብ ዋስትናን ለማረጋገጥ እየተሰራ መሆኑን የኦሮሚያና የማዕከላዊ ኢትዮጵያ ክልሎች የግብርና ቢሮ አመራር አባላት ገለፁ።

የኦሮሚያ ግብርና ቢሮ ምክትል ሃላፊ አቶ በሪሶ ፈይሳ ለኢዜአ እንደገለጹት በክልሉ አምስት ዞኖች ላይ የእንሰት ልማትን ለማስፋፋት እየተሰራ ነው።

በተለይ በሁለቱ የጉጂ ዞኖች፣ በደቡብ ምዕራብ ሸዋ፣ በጅማ እና ሌሎች ዞኖች ላይ የእንሰት ልማት በስፋት እየተከናወነ መሆኑን አስረድተዋል።

ባለፉት ዓመታት የእንስት ልማት በክልሉ ትኩረት እንዳላገኘ ያስታወሱት አቶ በሪሶ፣ "በዘንድሮው ዓመት ከሁለት ሚሊዮን በላይ የእንሰት ችግኞች ተዘጋጅተው ለአርሶ አደሩ እየተሰራጨ ነው" ብለዋል።

የእንሰት ልማቱን ወደ ሌሎች የክልሉ ዞኖች ለማስፋፋት ለህብረተሰቡ ግንዛቤ የማስጨበጥ ሥራም ጎን ለጎን  እየተሰራ መሆኑን አመልክተዋል።

በምክትል ርዕሰ መስተደድር ማዕረግ የማዕከላዊ ኢትዮጵያ ግብርናና ገጠር ልማት አስተባባሪና የግብርና ቢሮ ሃላፊ አቶ ኡስማን ሱሩር በበኩላቸው እንደገለጹት፣ ሀገራዊ የእንሰት ልማት ፕሮግራምን መሰረት በማድረግ በክልሉ የእንሰት ተክልን ከመጥፋት ወደ ማስፋፋት ደረጃ ማምጣት ተችሏል።

እንሰት ለሰው ልጅ ለምግብና ለጤና ካለው የጎላ ጠቀሜታ በተጨማሪ የአፈር ለምነትን በመጠበቅ ረገድ የማይተካ ሚና አለው ብለዋል።

አርሶ አደሩ ተገቢውን ግንዛቤ አግኝቶ የእንሰት ተክልን እንዲያለማ በክልሉ "እንሰትን ከመጥፋት ወደ ማስፋፋት" በሚል መርህ ንቅናቄ እየተካሄደ ነው ብለዋል።

እንሰት ድርቅን ጨምሮ የአየር ንብረት ለውጥ የሚያስከትለውን ተፅዕኖ የሚቋቋምና እርጥበትን አምቆ ለረዥም ጊዜ የሚያቆይ በመሆኑ በእንሰት ልማት ላይ ትኩረት ተሰጥቶ እየተሰራ መሆኑን ተናግረዋል።

"በዘንድሮው ዓመት ብቻ በክልሉ ከ87 ሚሊዮን በላይ የእንሰት ችግኞችን አሰራጭተናል" ያሉት አቶ ኡስማን እስካሁንም ከ37 ሺህ ሄክታር በላይ መሬት በእንሰት ተክል መሸፈኑን ገልጸዋል።

እንሰት ለአካባቢያዊ ስነ ምህዳር ጥበቃ ፋይዳው የጎላ መሆኑን ጠቅሰው፣ ከሌሎች የሰብልና ፍራፍሬ ዝርያዎች ጋር በጣምራ መልማት የሚችል ተክል መሆኑንም አስረድተዋል።

በሀገር አቀፍ ደረጃ የእንሰት ልማት ስትራቴጂ ተዘጋጅቶ ወደ ትግበራ መገባቱን ለማወቅ ተችሏል።

 

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም