ሠራዊቱ ከዋናው ተልዕኮው ባሻገር የህዝብን ማህበራዊ ችግሮች ለማቃለል የድርሻውን እየተወጣ ነው

ድሬዳዋ፤ ሰኔ 4/2016(ኢዜአ)፡- የአገር መከላከያ ሠራዊት የአገርን ሉዓላዊነት ከማስከበር ተልዕኮው ጎን ለጎን ማህበራዊ ችግሮችን በሚያቃልሉ ተግባራት ላይ የድርሻውን እየተወጣ መሆኑን የሁርሶ ኮንቲንጀንት  ማሰልጠኛ ትምህርት ቤት ምክትል አዛዥ ሌተናል ኮሎኔል ገነነው ቶላ ገለጹ።

የማሰልጠኛ ትምህርት ቤቱ  በምሥራቅ ሐረርጌ ዞን ሜታ ወረዳ ለሰርከማ ቀበሌ ማህበረሰብ ከሶስት ኪሎ ሜትር በላይ የውስጥ ለውስጥ ጥርጊያ መንገድ ሰርቶ አስረክቧል።

የትምህርት ቤቱ ምክትል አዛዥና የስልጠና ኃላፊ ተወካይ ሌተናል ኮሎኔል ገነነው ቶላ እና ከፍተኛ ወታደራዊ መኮንኖች በምልምል ሠራዊት ሰልጣኞች የተሰራውን መንገድ ለማህበረሰቡ አስረክበዋል።

በርክክብ መርሃ ግብሩ ላይ  ሌተናል ኮሎኔል ገነነው እንደተናገሩት ፤ የአገር መከላከያ ሠራዊት የኢትዮጵያ ሉዓላዊነት እና ዳር ድንበር ከመቼውም ጊዜ በላይ በአስተማማኝ ወኔና ትጋት እያስከበረ ይገኛል።

ከዚህ ጎን ለጎን ሠራዊቱ በሚገኝባቸው አካባቢዎች የሚስተዋሉ ማህበራዊ ችግሮችን በማቃለል ህዝባዊ ወገንተኝነቱን በተግባር እያረጋገጠ እንደሚገኝ አመልክተዋል።

በሁርሶ የኮንቲንጀንት ማሰልጠኛ ትምህርት ቤት በሚጎራበተው የሜታ ወረዳ ለሰርከማ ቀበሌ ማህበረሰብ ሰርቶ ያስረከበው የውስጥ ለውስጥ የጥርጊያ መንገድም የዚሁ ተግባሩ ማሳያ መሆኑን አውስተዋል።

መንገዱ ተሰርቶ ለአገልግሎት መዋሉ ቀደም ሲል ወላድ እናቶች እና አረጋዊያን ህክምና ለማግኘት ሲገጥማቸው የነበሩትን ችግሮች ይፈታል ብለዋል።

የማሰልጠኛው ትምህርት ቤት የኮሙኒኬሽን ዴስክ ኃላፊ ሻለቃ ገመቹ አሰፋ በበኩላቸው፤ ሠራዊቱ ከዋናው ተልዕኮ ጎን ለጎን የእናቶችና ህፃናትን ህይወት ለመታደግ ደም በመለገስ፣ ለታላቁ የህዳሴ ግድብ ቦንድ በመግዛት፣ ለችግረኞች ማዕድ በማጋራትና የአረጋውያንን ቤቶች በመጠገን ማህበራዊ ኃላፊነቱን እየተወጣ መሆኑን አስረድተዋል።


 

በሰራዊቱና በህዝብ ቅንጅት በመተግበር ላይ የሚገኙት ማህበራዊ ልማቶችም የሠራዊቱንና የህዝቡን ትስስርና አንድነት በፀና መሠረት ላይ እንዲጠናከር ማድረጋቸውን ነው የገለፁት።

በቀጣይም ሠራዊቱ ተልዕኮውን በአስተማማኝ መንገድ ከመወጣት ባሻገር መሰል ማህበራዊ ተግባራትን ያጠናክራል ብለዋል።

መንገዱ አገልግሎት የጀመረበት የሜታ ወረዳ የጤና ቢሮ ኃላፊና የወረዳው ተወካይ አቶ ሻፊ አደም ሠራዊቱ ከማህበረሰቡ ጋር ተቀናጅቶ እያከናወናቸው የሚገኙት ማህበራዊ ልማቶች የህዝብን አንገብጋቢ ችግሮች እያቃለሉ መሆናቸውን ተናግረዋል።


 

በሠራዊቱ ተገንብቶ አገልግሎት መስጠት የጀመረው መንገድ ለተሽከርካሪዎች ምቹ በመሆኑ ቀደም ሲል በትራንስፖርት እጥረት ይፈጠር የነበረን የእናቶችና የህፃናት ጉዳት ያስቀራል ብለዋል።

ሠራዊቱ ከተልዕኮው ጎን ለጎን የማህበረሰቡን ችግሮች በተቀናጀ ቁርጠኝነትና ፍጥነት በማቃለል ህዝባዊነቱን በትክክል እያረጋገጠ እንደሚገኝ የገለፁት ደግሞ የሰርከማ የገጠር ቀበሌ ሊቀ መንበር አቶ ሙዲን መሐመድ ናቸው።

የሰርከማ ገጠር ቀበሌ ነዋሪዎች በመንገዱ መሰራት የተሰማቸውን ደስታ መግለፃቸውን የትምህርት ቤቱ የኮሙኒኬሽን ዴስክ ለኢዜአ በላከው መረጃ አመላክተዋል።

 

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም