የተቀናጀ የውሃ ሐብት አስተዳደርን እውን ለማድረግ የባለድርሻ አካላት ትስስር ሊኖር ይገባል - የአዋሽ ተፋሰስ አስተዳደር ፅህፈት ቤት


ሠመራ ፤ ሰኔ 4 /2016 (ኢዜአ)፡- የተቀናጀ የውሃ ሐብት አስተዳደርን እውን ለማድረግ የባለድርሻ አካላት ትስስር ሊኖር እንደሚገባ የአዋሽ ተፋሰስ አስተዳደር ፅህፈት ቤት  አስታወቀ።

ዛሬ በሠመራ ከተማ በአዋሽ ተፋሰስ የንዑስ ተፋሰስ የባለድርሻ አካላት 'ኘላትፎርም' ምስረታ መድረክ እየተካሄደ ነው።

በዚህ መድረክ ላይ የተገኙት የአዋሽ ተፋሰስ አስተዳደር ፅህፈት ቤት ሃላፊ አቶ አደን አብዶ እንዳሉት የተቀናጀ የውሃ ሃብት አስተዳደርን ዕውን ማድረግ የሚቻለው በተፋሰሱ ውስጥ በውሃ ላይ የሚሰሩ ባለድርሻ አካላት ትስስር ሲኖር ነው። 

በውሃና ከውሃ ጋር ተያያዥነት ባላቸው የስራ ዘርፍ ላይ የተሰማሩ ባለድርሻ አካላት ትስስር ሲኖር ነው።

በዚህም የተቀናጀ አሰራር ከመዘርጋት ባለፈ የጋራ ራዕይ ባለው የተፋሰስ ዕቅድ መመራትና ለተግባራዊነት መትጋት ያስፈልጋል ብለዋል።

ከዓባይ ተፋሰስ ቀጥሎ በአገሪቱ ካሉ ተፋሰሶች መካከል የአዋሽ ተፋሰስ ተጠቃሽ መሆኑን ገልጸዋል።


 

ተፋሰሱ ካለው የመልማት አቅም፣ ካለው የቆዳ ስፋት እንዲሁም ከሌሎች አገራዊና አለም ዓቀፋዊ ጉዳዮች አንፃር በአገራችን ካሉ 12 ተፋሰሶችና ሐይቆች ግንባር ቀደም መሆኑንም ጠቅሰዋል።

ከጊንጪ ዳገቶች መነሻ አድርጎ 1ሺህ 200 ኪሎ ሜትር ተጉዞ ጅቡቲ ድንበር አካባቢ በአፋምቦ ሐይቅ መዳረሻውን የሚያደርገው የአዋሽ ወንዝ ተፋሰስ ካለው አብዛኛው የቆዳ ስፋት ለልማት የሚውል መሆኑንም አውስተዋል።

ከተፋሰሱ ከ200ሺህ ሄክታር በላይ የሚሆነው በመስኖ እየለማ እንደሚገኝ የገለፁት አቶ አደን፤ በተጨማሪም ለመጠጥ ውሃ አገልግሎት፣ ለሃይድሮ ፖወር፣ ለእንስሳትና ዓሣ ሃብት እንዲሁም ለቱሪዝም መስህብነት እየዋለ እንደሚገኝ ተናግረዋል።

"ይሄን ሐብት ጠብቆ የማቆየት እና የተሻለ ጠቀሜታ እንዲሰጥ ማድረግ የባለድርሻ እና የአጋር አካላት ሚና ነው" ብለዋል።

መንግስት የህብረተሰቡን የልማት ፍላጎት እውን ለማድረግ ስትራቴጂን መነሻ በማድረግ የውሃ ሐብት ዘርፉን የሚያሻሽሉ ተግባራትን እየተገበረ መሆኑንም ነው አቶ አደን የገለፁት።

በዚሁ መድረክ ላይ የመወያያ ፅሁፍ ያቀረቡት የላይኛው አዋሽ ቤዝን አስተዳደር ፅህፈት ቤት ሃላፊ አቶ  አብርሃም ዲርባባ በበኩላቸው ከተፈጥሮ ሃብቶቻችን ውስጥ ውሃ ዋነኛው ነው ብለዋል።

የአዋሽ ተፋሰስን በአግባቡ ለመጠቀም የሚያስችሉ ውሃን ማዕከል ያደረጉ የውሃ ሃብት አስተዳደር ሃላፊነት  አንጻር በጋራ በመሆን መሠራት እንደሚገባ ነው የገለፁት።

አሁን ላይ እንደ አገር እየታየ ያለውን የህዝብ ብዛት መጨመርን ተከትሎ ያለንን የውሃ ሀብት በአግባቡ መጠቀም እንደሚገባም ነው የተናገሩት።

በዚህ መድረክ ላይ የውሃና ኢነርጂ ሚኒስቴር፣ የአዋሽ ተፋሰሰ፣ የኦሮሚያ ክልልና አፋር ክልል እንዲሁም የአዲስ አበባ አስተዳድር ባለድርሻ አካላት ታድመዋል።

 

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም