ምክር ቤቱ የፌዴራል መንግስት ግዢና ንብረት አስተዳደር እና የሕዝብ በዓላትንና የበዓላትን አከባበር ለመወሰን የቀረቡ ረቂቅ አዋጆችን አፀደቀ

አዲስ አበባ፤ ሰኔ 4/2016(ኢዜአ)፦ የህዝብ ተወካዮች ምክር ቤት ዛሬ ባካሄደው 3ኛ የስራ ዘመን 31ኛ መደበኛ ስብሰባው የፌዴራል መንግስት ግዢና ንብረት አስተዳደር እና የሕዝብ በዓላትንና የበዓላትን አከባበር ለመወሰን የቀረቡ ረቂቅ አዋጆችን አጽድቋል።

ምክር ቤቱ የተለያዩ ረቂቅ አዋጆችን ለሚመለከታቸው ቋሚ ኮሚቴዎች መርቷል።

የፌዴራል መንግስት ግዢና ንብረት አስተዳደር አዋጅ የመንግሥት የግዥና ንብረት አስተዳደርን ከቴክኖሎጂ ለውጥ ጋር ማራመድ የሚያስችሉ ድንጋጌዎችን ያካተተ መሆኑ ተገልጿል።

የሕዝብ በዓላትንና የበዓላትን አከባበር አዋጅ ለዜጎች ስነ-ምግባርና ስነ-ልቦና ግንባታ እንዲሁም ለሀገርና ለህዝብ ያላቸው ማህበራዊና ኢኮኖሚያዊ ፋይዳ ከፍተኛ መሆኑ ተነስቷል።


 

የንብረት ማስመለስ፣ በወንጀል የተገኘ ንብረት ህጋዊ ማስመሰልና ሽብርተኝነትን በገንዘብ የመርዳት ወንጀልን ለመከላከልና ለመቆጣጠር እንዲሁም የነዳጅ ውጤቶችን ግብይት ስርዓት ለመደንገግ የቀረቡ ረቂቅ አዋጆች ለሚመለከታቸው ቋሚ ኮሚቴዎች ተመርተዋል።

ምክር ቤቱ ከሰዓት በኃላ የገንዘብ ሚኒስትሩ አህመድ ሽዴ የፌዴራል መንግስት የ2017 በጀት አመት ረቂቅ በጀትን በተመለከተ በሚያቀርቡት መግለጫ ላይ በመወያየት ረቂቅ የበጀት አዋጁን ለዝርዝር እይታ ለፕላን፣ በጀትና ፋይናንስ ጉዳዮች ቋሚ ኮሚቴ ይመራል ተብሎ ይጠበቃል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም