ባለፉት አሥር ወራት በዋና ዋና የማክሮ ኢኮኖሚ ዘርፎች የተመዘገበው ስኬት የ7 ነጥብ 9 በመቶ እድገት እንደሚመዘገብ አመላካች ነው

አዲስ አበባ፤ ሰኔ 4/2016(ኢዜአ)፦ ባለፉት አሥር ወራት በዋና ዋና የማክሮ ኢኮኖሚ ዘርፎች የተመዘገበው ስኬት የ7 ነጥብ 9 በመቶ እድገት እንደሚመዘገብ አመላካች መሆኑ ተገለጸ።

የበጀት ዓመቱ የመጨረሻው የ100 ቀናት አፈጻጸም ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ(ዶ/ር) በተገኙበት እየተካሄደ ነው።

የፕላንና ልማት ሚኒስትር ፍጹም አሰፋ(ዶ/ር) በመድረኩ ያለፉት 100 ቀናት እና የሁለተኛው ሀገር በቀል ኢኮኖሚ አፈጻጸም እንዲሁም የ2017 በጀት ዓመት የትኩረት አቅጣጫዎች ላይ ሪፖርት አቅርበዋል።

በዚህም ባለፉት አሥር ወራት የ3 ነጥብ 2 ቢሊዮን ዶላር የውጭ ቀጥታ ኢንቨስትመንት መሳብ መቻሉን ተናግረዋል።

ይህም ካለፈው ዓመት ተመሳሳይ ወቅት ጋር ሲነጻጸር የ14 ነጥብ 3 በመቶ ብልጫ እንዳለው ተናግረዋል።

በተጨማሪም መንግሥት 425 ቢሊዮን ብር ገቢ መሰብሰቡን ገልጸው፤ ከዚህም ውስጥ 271 ቢሊዮን ብሩ ከሀገር ውስጥ ገቢ የተሰበሰበ ነው።

ከሸቀጦች የወጪ ንግድ 2 ነጥብ 9 ቢሊዮን ዶላር መገኘቱንም እንዲሁ።


 

በተጨማሪም ከሬሚታንስ 4 ነጥብ 2 ቢሊዮን ዶላር መገኘቱን የተናገሩት ሚኒስትሯ፤ የመንግሥት የበጀት ጉድለትም ካለፈው ዓመት ተመሳሳይ ወቅት ጋር ሲነጻጸር በ14 በመቶ መቀነስ መቻሉን ገልፀዋል።

በተጠቀሰው ወራት ለ2 ነጥብ 5 ሚሊዮን ዜጎች በሀገር ውስጥ እንዲሁም ከ300 ሺህ በላይ ለሚሆኑት ደግሞ በውጭ ሀገራት የሥራ ዕድል ተፈጥሯል ብለዋል።

በአጠቃላይ በዋና ዋና የማክሮ ኢኮኖሚ አመላካቾች የተመዘገበው ስኬት ኢትዮጵያ የ7 ነጥብ 9 በመቶ እድገት እንደምታስመዘግብ አመላካች መሆኑን አብራርተዋል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም