በመጪው ክረምት ለ60 ሺህ የ2ኛ ደረጃ ትምህርት ቤት መምህራንና የትምህርት ቤት አመራሮች ስልጠና ሊሰጥ ነው-ትምህርት ሚኒስቴር - ኢዜአ አማርኛ
በመጪው ክረምት ለ60 ሺህ የ2ኛ ደረጃ ትምህርት ቤት መምህራንና የትምህርት ቤት አመራሮች ስልጠና ሊሰጥ ነው-ትምህርት ሚኒስቴር
አዲስ አበባ፤ ሰኔ 4/2016(ኢዜአ)፦በመጪው ክረምት ለ60 ሺህ የ2ኛ ደረጃ ትምህርት ቤት መምህራንና የትምህርት ቤት አመራሮች የአቅም ማጎልበቻ ስልጠና ሊሰጥ መሆኑን ትምህርት ሚኒስቴር ገለጸ።
ትምህርት ሚኒስቴር ከኮተቤ የትምህርት ዩኒቨርሲቲ ጋር በመተባበር ከዛሬ ሰኔ 04/2016 ዓ.ም ጀምሮ ለሶስት ተከታታይ ቀናት የሚቆይ ለመምህራንና የትምህርት ቤት የስራ ኃላፊዎች የሚሰጠውን የክረምት ወራት የአሰልጣኞች ስልጠና አስጀምሯል።
የትምህርት ሚኒስትር ዴኤታ አየለች እሸቴ በዚሁ ወቅት፥ የትምህርት ቤቶችን ደረጃ የማሻሻልና የትምህርት ተደራሽነትን ፍትሕዊ የማድረግ ስራ ትኩረት ተሰጥቶታል ብለዋል።
ከሁሉም በላይ በዘርፉ ብቁ የሰው ኃይል ስምሪት በመስጠት የትምህርት ጥራትን ለማረጋገጥ ጥረት እየተደረገ መሆኑንም ጠቁመዋል።
የመምህራንና የትምህርት ዘርፍ መሪዎችን እውቀት መር አቅም ለማጎልበት በመጪው ክረምት ዕውቀትና ክህሎትን ማሳደግ የሚያስችል ስልጠና ለመስጠት ዝግጅት መደረጉንም ገልጸዋል።
በ28 የመንግስት ከፍተኛ ትምህርት ተቋማት አማካይነት ለ60 ሺህ የ2ኛ ደረጃ ትምህርት ቤት የሒሳብ፣ ሳይንስና እንግሊዝኛ መምህራንና የትምህርት ቤት አመራሮች ስልጠና እንደሚሰጥ ተናግረዋል።
የኮተቤ የትምህርት ዩኒቨርሲቲ ፕሬዚዳንት ብርሃነ-መስቀል ጠና (ዶ/ር)፤ በትምህርት ዘርፉ ያጋጠመውን ስብራት በመጠገን በዕውቀትና ክህሎት የዳበረ ትውልድ ለማፍራት በትብብር መስራት ወሳኝ ነው ብለዋል።
የትምህርት ዘርፉ ስብራትን ለመጠገን የመምህራንና የትምህርት ኃላፊዎችን ዕውቀትና ክህሎት ማጎልበት የሚያስችል ስልጠና ለመስጠት መዘጋጀታቸውን አረጋግጠዋል።
መምህራንና የትምህርት ቤት የስራ ኃላፊዎች የሚሰጣቸውን ስልጠና ወደ ተግባር በመቀየር የትምህርት ጥራትን ለማስጠበቅ ሚናቸውን መወጣት እንደሚገባቸው አስገንዝበዋል።
በኮተቤ የትምህርት ዩኒቨርሲቲ ለሶስት ተከታታይ ቀናት በሚሰጠው የአሰልጣኞች ስልጠና ላይ 224 አሰልጣኞች እንደሚሳተፉ ተገልጿል።