ቀጥታ፡

የሚያስተሳስር የጋራ ትርክት ለመገንባት በሚደረገው እንቅስቃሴ የመገናኛ ብዙሃንና ኮሙኒኬሽን ባለሞያዎች ሚና ወሳኝ ነው - አቶ አዲሱ አረጋ

ሀዋሳ፤ ሰኔ 4/2016 (ኢዜአ)፡- የሚያስተሳስር የጋራ ትርክትን ለመገንባት በሚደረገው እንቅስቃሴ የመገናኛ ብዙሃንና ኮሙኒኬሽን ባለሞያዎች ሚና ወሳኝ መሆኑን የብልጽግና ፓርቲ የህዝብና ዓለም አቀፍ ግንኙነት ዘርፍ ሃላፊ አቶ አዲሱ አረጋ አስገነዘቡ።

"የብሔራዊነት ትርክት ለኢትዮጵያ ልዕልና" በሚል መሪ ሀሳብ ለመገናኛ ብዙሃንና ኮሙኒኬሽን ባለሙያዎች የተዘጋጀ ስልጠና በሀዋሳ ተጀምሯል።

በስልጠናው መክፈቻ ላይ የብልጽግና ፓርቲ የህዝብና ዓለም አቀፍ ግንኙነት ዘርፍ ሃላፊ አቶ አዲሱ አረጋ እንዳሉት የብልጽግና ፓርቲ በሀገሪቱ የህዝቦች የዘመናት ጥያቄ የሆነውን የተሟላ ዴሞክራሲ ለማስፈን አበክሮ እየሰራ ነው ።

በዚህ ረገድ የመገናኛ ብዙሃንና ኮሙኒኬሽን ባለሙያዎች አንድ የሚያደርጉና የሚያስተሳስሩ የጋራ ትርክቶችን ለመገንባት በሚደረገው እንቅስቃሴ የማይተካ ሚና አላቸው ብለዋል።

በተለይም በህዝቦች መካከል መግባባትና የጋራ አንድነት እንዲኖር ለማድረግና የሀሳብ የበላይነትን ለማምጣት ልዩ ትኩረት ሰጥተው መስራት እንደሚጠበቅባቸው ጠቅሰዋል።


 

ለዚህ ደሞ የጋራ ትርክት እንዲኖር በማድረግ አፍራሽ ፕሮፓጋንዳን መመከት የሚያስችል ቋሚ አጀንዳ ሊኖራቸው ይገባል ነው ያሉት።

ህብረ ብሔራዊ አንድነትን ለማረጋገጥ በህዝቦች መካከል ልዩነት የሚያመጡ ጉዳዮችን በመመከት ገዢና አሰባሳቢ ትርክት ላይ በማተኮር መስራት የመገናኛ ብዙሃንና ኮሙኒኬሽን ባለሙያዎች ትልቅ ሀላፊነት መሆኑን አሳስበዋል።

በብልጽግና ፓርቲ የሲዳማ ቅርንጫፍ ጽህፈት ቤት የፖለቲካና አቅም ግንባታ ዘርፍ ሀላፊ አቶ አስፋው ጎኒሶ በበኩላቸው የህዝቦችን አንድነትና ትስስር ለማጽናት የመገናኛ ብዙሃን አካላት ያላቸው ፋይዳ የላቀ መሆኑን ጠቁመዋል።

ይህንን መሳሪያ በመጠቀም የመገናኛ ብዙሃንና ኮሚኒኬሽን ባለሙያዎች የኢትዮጵያ ህዝቦች በጋራ ተጋግዘው እንዲኖሩ ለማድረግ ገዢ ትርክት ላይ ማተኮር እንደሚገባቸው በመጠቆም።

ለአምስት ቀናት በተዘጋጀው በዚሁ ስልጠና መድረክ ላይ ከሲዳማ፣ ደቡብ ኢትዮጵያ፣ ኦሮሚያና ማዕከላዊ ኢትዮጵያ ክልሎች የተውጣጡ ባለሙያዎችና አመራሮች እየተሳተፉ ይገኛሉ።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም