ኢትዮጵያ ሰላምን፣ ሁሉን አቀፍ ዘላቂ ልማትንና ውጤታማ ባለብዙ ወገን ግንኙነትን በጋራ ለማስፈን ቁርጠኛ ነች - አምባሳደር ታዬ አጽቀስላሴ

አዲስ አበባ፤ ሰኔ 4/2016(ኢዜአ)፦ኢትዮጵያ ሰላምን፣ ሁሉን አቀፍ ዘላቂ ልማትንና ውጤታማ ባለብዙ ወገን ግንኙነትን በጋራ ለማስፈን ቁርጠኛ  መሆኗን አምባሳደር ታዬ አጽቀስላሴ ገልጸዋል።

አምባሳደር ታዬ አጽቀሥላሴ ከሰኔ 3-4 ቀን 2016 ዓ.ም በሩሲያ ፌዴሬሽን ኒዥኒ ኖቭጎሮድ ውስጥ በሚካሄደው የብሪክስ የውጭ ጉዳይ እና ዓለም አቀፍ ግንኙነት ሚኒስትሮች ስብሰባ ላይ በመሳተፍ ላይ ይገኛሉ።

ሚኒስትሩ በመድረኩ ባደረጉት ንግግር ኢትዮጵያ ለብሪክስ አባልነቷ ትልቅ ቦታ እንደምትሰጥ በአፅንኦት መግለጻቸውን ከውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር የተገኘው መረጃ ያመላክታል።

ኢትዮጵያ በብሪክስ ውስጥ ያላትን የጎላ ሚና ለማሳደግም ከብሔራዊ የልማት ትኩረቶቿ አኳያ የተወሰዱ የተለያዩ እርምጃዎችንም አብራርተዋል።


 

ኢትዮጵያ ሰላምንና እድገትን፣ ሁሉን አቀፍና ዘላቂ ልማትን እንዲሁም ውጤታማ ባለብዙ ወገን ግንኙነትን በጋራ ለማስፈን ቁርጠኛ መሆኗንም የውጭ ጉዳይ ሚኒስትሩ አምባሳደር ታዬ አጽቀስላሴ ገልጸዋል።

ወቅታዊ እና አንገብጋቢ የሆኑ ድንበር ዘለል አለም አቀፋዊ ጉዳዮችም በየትኛውም ተቋም ለብቻ ሊፈቱ ስለማይችሉ እውነተኛ ዓለም አቀፋዊ አጋርነት የምርጫ ጉዳይ ብቻ ሳይሆን አስፈላጊ መሆኑን ጠቁመዋል። 

ልማትን በዓለም አቀፍ ደረጃ ማዕከል ያደረጉ እና የጋራ መፍትሄዎችን የሚያመላክቱ ውጤታማ የባለብዙ ወገን ግንኙነቶች በስበሰባው አፅንኦት እንደተሰጣቸውም ተመላክቷል።

የታዳጊ ሀገራትን ጥቅም ለማስጠበቅም የባለብዙ ወገን ተቋማትን መልሶ ማቋቋም፣ የልማት ፋይናንስ እና የእዳ ስረዛ ማሳደግ አስፈላጊ መሆኑን ሚኒስትሩ አሳስበዋል። 

በተጨማሪም ኢትዮጵያ ሰላምን እና እድገትን፣ ሁሉን አቀፍ እና ዘላቂ ልማትን እንዲሁም ውጤታማ ባለብዙ ወገን ግንኙነትን በጋራ ለማስፈን ቁርጠኛ መሆኗን አረጋግጠዋል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም