በምዕራብ ጎንደር ዞን የተፈጥሮ ደን በተደራጁ ማህበራትና ባለሃብቶች ጥበቃ እየተደረገለት ነው - ኢዜአ አማርኛ
በምዕራብ ጎንደር ዞን የተፈጥሮ ደን በተደራጁ ማህበራትና ባለሃብቶች ጥበቃ እየተደረገለት ነው
መተማ፤ ሰኔ 04/2016 (ኢዜአ)፦በምዕራብ ጎንደር ዞን 300 ሺህ ሄክታር የሚጠጋ የተፈጥሮ ደን ተከልሎ በተደራጁ ማህበራትና ባለሃብቶች ጥበቃ እየተደረገለት መሆኑን የዞኑ ደንና አካባቢ ጥበቃ ተጠሪ ጽህፈት ቤት አስታወቀ።
የጽህፈት ቤቱ ኃላፊ አቶ ደግነት አበበ እንደተናገሩት በዞኑ ከ750 ሺህ ሄክታር በላይ መሬት በተፈጥሮ ደን የተሸፈነ ነው።
ይሁን እንጂ በእርሻ ሥራ መስፋፋት፣ ለከሰል፣ ለቤት ቤት መስሪያና ሌሎች ምክንያቶች በደን ሀብቱ ላይ ጉዳት እየደረሰ መምጣቱን ተናግረዋል።
በደን ላይ የሚደርሰውን ጉዳት ለመከላከል ከተከለለው ጥብቅ ደን በተጨማሪ 300 ሺህ ሄክታር የሚጠጋ ደን በ36 ማህበራትና ባለሃብቶች እየተጠበቀ መሆኑን አስረድተዋል።
ማህበራቱ ደኑ ካፈራው ሀብት እየተጠቀሙ ከውድመት እንዲከላከል በማድረጋቸውም የደን ጭፍጨፋው መቀነሱን ኃላፊው ተናግረዋል።
በተደራጀ መንገድ እንዲጠበቅ በተደረገው የደን ሀብትም እጣንና ሙጫን በማምረት በዓመት እስከ 150 ሚሊዮን ብር የሚደርስ ገቢ እየተገኘ መሆኑን አቶ ደግነት ገልጸዋል።
ከማህበራትና ባለሃብቶች በተጨማሪ የደን ጭፍጨፋን ለመከላከልና ለመጠበቅ የሚያግዝ የደን ጥበቃ ግብረ ኃይል በወረዳዎች ተቋቁሞ የጥበቃና መከላከል ስራ እየተከናወነ መሆኑን አስረድተዋል።
ግብረ ኃይሉ ባደረገው ቅንጅታዊ ጥረትም ደን ሲጨፈጭፉ የተገኙ 27 ግለሰቦች ፍርድ ቤት ቀርበው እስከ ስድስት ዓመት በሚደርስ እስራት መቀጣታቸውን ገልጸዋል።
በቋራ ወረዳ የአዲስ ዓለም ቀበሌ ነዋሪ አርሶ አደር ሲሳይ አላምረው እንዳሉት በዘላቂ የተፈጥሮ ሀብት ልማት በማህበር ተደራጅተው የደን ሀብቱን በባለቤትነት እየተንከባከቡ ነው።
አካባቢው በደን ሀብት የታደለ ቢሆንም፤ ቀደም ሲል ጥበቃና እንክብካቤ ሳይሰጠው በመቆየቱ መሬቱ ለመራቆት መጋለጡን አስታውሰዋል።
አሁን ግን የደን ሀብቱን በመጠበቅና በመንከባከብ ይደርስበት ከነበረው ጭፍጨፋ ለመታደግ ከመቻሉም በላይ፤ እጣንና ሙጫ በመሰብሰብ በዓመት በግል ከ100 ሺህ ብር በላይ ገቢ ማግኘት መቻላቸውን ገልጸዋል።
በመተማ ወረዳ የሽመለ ጋራ ቀበሌ ነዋሪ አርሶ አደር ብርቁ መርሻ በበኩላቸው ተከልሎ የተሰጣቸው የተፈጥሮ ደን ተደራጀው እየጠበቁና እየተንከባከቡ መሆኑን ተናግረዋል።
በአካባቢው የነበረው ደን ለመኖሪያ ቤት መስሪያ ተፈላጊ በመሆኑ በብዛት ይቆረጥ እንደነበር አስታውሰው፤ አሁን ላይ በሚያደርጉት ጥበቃ ጉዳቱን መቀነስ እንደተቻለ ገልጸዋል።
በቀጣይም ለኅብረተሰቡ የደን ጭፍጨፋ የሚያደርሰውን ጉዳት በማሳወቅ በጥበቃና እንክብካቤ እንዲሳተፍ ጥረት አደርጋለሁ ብለዋል።
በዞኑ የአልጣሽ ብሄራዊ ፓርክ እና ማህበረ ስላሴ አንድነት ገዳም ጥብቅ ደን እንደሚገኙም ይታወቃል።