የገንዘብ ሚኒስትር አህመድ ሽዴ ከኳታር አቻቸው ጋር ተወያዩ

አዲስ አበባ፤ ሰኔ 3/2016(ኢዜአ)፦የገንዘብ ሚኒስትር አቶ አህመድ ሽዴ ከኳታሩ የገንዘብ ሚኒስትር አሊ ቢን አህመድ አል ኩዋሪ /Ali bin Ahmed Al Kuwari/ ጋር ተወያዩ።

በኳታሩ የገንዘብ ሚኒስትር ጽሕፈት ቤት ባደረጉት ውይይትም በሁለቱ ሀገሮች መካከል በፋይናንስ፣ በልማት ትብብር እና በኢንቨስትመንት ዙሪያ መክረዋል።

ሚኒስትሩ ኢትዮጵያ እደረገች ያለችውን የለውጥ እንቅስቃሴና የተገኙ ትሩፋቶችን እንዲሁም ለኳታር ኩባንያዎችና ባለሀብቶች ሀገራችን ያላትን የኢንቨስትመንት ዕድሎች በሰፊው ያብራሩ ሲሆን በተቋም ለተቋም ግንኙነቱም በትብብር ለመስራት ከስምምነት ደርሰዋል።

በቀጣናዊ እንዲሁም በዓለም አቀፋዊ መድረኮችም ላይ ከኳታር ጋር በትብብር ለመስራት የጋራ ሥምምነት ላይ መድረሳቸው ተገልጿል።

በሌላ በኩል ከልማት ፋይናንስ አኳያ የኳታር የልማት ፈንድ በኢትዮጵያ የጀመራቸውን ፕሮጀክቶች እንዲጠናከሩና ተጨማሪ ትብብሮችን መፍጠር እንዲቻል የቴክኒካል ቡድን ወደ ኢትዮጵያ ለመላክና አጠቃላይ ያሉትን ፍላጎቶች በመለየት ወደ ስራ ለመግባት ስምምነት ላይ መደረሱን ከዶሃ የኢትዮጵያ ኤምባሲ የተገኘው መረጃ ያመላክታል።

ኢትዮጵያና ኳታር ለረጅም ዘመናት የዘለቀ የመንግስትና የህዝብ ለህዝብ ግንኙነት ያላቸው ሃገራት ናቸው።

በሀገራቱ መካከል እ.ኤ.አ ኖቬምበር 2014 በዶሃ የመጀመሪያው የጋራ ምክክር የተደረገ ሲሆን ሁለተኛው ደግሞ ኢትዮ-ኳታር የጋራ ቴክኒካል ኮሚቴ ምክክር እ.ኤ.አ. ፌብሪዋሪ 2016 በአዲስ አበባ ከተማ ተካሂዷል።

ሦስተኛው የፖለቲካ የጋራ ምክክር በያዝነው በፈረንጆች ዓመት 2024 እንደሚደረግም ይጠበቃል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም