በክልሉ ብክለትን በመከላከል ብዝሃ ሕይወትን ለመጠበቅ የሚያስችሉ የግንዛቤ ማስጨበጥ ስራዎች ላይ ትኩረት ተደርጓል

ዲላ ፤ ሰኔ 3/2016 (ኢዜአ)፡- በደቡብ ኢትዮጵያ ክልል ብክለትን በመከላከል ብዝሃ ሕይወትን ለመጠበቅ የግንዛቤ ማስጨበጥ ስራ በዘመቻ መልክ እየተከናወነ መሆኑን የክልሉ ደን፣ አካባቢ ጥበቃና ልማት ቢሮ ገለጸ።

ዓለም አቀፍ የአካባቢ ቀን "የመሬት ማገገም በረሃነትንና ድርቅን ለመቋቋም" በሚል መሪ ቃል በክልል ደረጃ በዲላ ከተማ ዛሬ ተከብሯል።

የቢሮው ኃላፊ አቶ ግዛቴ ግጄ በወቅቱ ለኢዜአ እንደተናገሩት፤ አካባቢ ጥበቃ መሬትን፣ ውሃንና አየርን ከብክለት በመከላከል የብዝሃ ሕይወት ደህንነትን ማስጠበቅ ነው።

በክልሉ የአካባቢ ብክለት በተለይ የመሬት ጉዳት በረሃማነትንና ድርቅን ከማስከተል ባለፈ በግብርና ምርታማነት ላይ የሚያደርሰውን ተፅዕኖ ለመቀነስ ዘርፈ ብዙ ተግባራት እየተከናወኑ መሆኑን ጠቅሰዋል።

በተለይ ብክለትን በመከላከል ብዝሃ ሕይወትን ለመጠበቅ የሚያስችሉ የግንዛቤ ማስጨበጫ ስራዎች በዘመቻ መልክ እየተከናወኑ እንደሚገኙ ተናግረዋል።

''መሬትን በአግባቡ ስንጠብቅ ውሃና መሰረተ ልማትን እየተንከባከብን ነው'' ያሉት ኃላፊው ''ይህንኑ ታሳቢ ያደረጉ የተራራ ልማት ስራዎች በክልሉ ሁሉም አካባቢዎች ተግባራዊ እየተደረጉ ነው'' ብለዋል።

በተለይ በክልሉ የሚገኙ 32 ከተሞች ጽዱና ለነዋሪዎች ምቹ እንዲሆኑ የጽዳት ባህልን የሚቀይሩና የአረንጓዴ ልማት ስራዎችን የሚያጎለብቱ ተግባራት በህዝብ ተሳትፎ እየተከናወኑ መሆኑንም አንስተዋል።

የጌዴኦ ባህላዊ የአካባቢ ጥበቃ ስርዓት ብዝሃ ሕይወት እንዲጠበቅ ማስቻሉን ያነሱት ደግሞ የጌዴኦ ዞን ዋና አስተዳዳሪ ዶክተር ዝናቡ ወልዴ ናቸው።

የተቀናጀ የአካባቢ ጥበቃ ተግባራትን፣ በተለይ ጥምር ግብርናውን ከፍራፍሬና ቡና ልማት ጋር በማስተሳሰር ዘላቂነቱንና የአርሶ አደሩን ተጠቃሚነት በሚያረጋግጥ መልኩ እየተተገበረ መሆኑን አመልክተዋል።

በተለይ ባህላዊ ስርዓቱ በዩኔስኮ መመዝገቡ የቱሪስት ፍሰቱን በማሳደግና ከካርበን ንግድ አርሶ አደሩን ተጠቃሚ ለማድረግ የጥናት ስራዎች በቅንጅት እየተከናወኑ መሆኑን አስረድተዋል።

ከተሞች የዞኑ የአካባቢ ጥበቃ ባህል መገለጫ እንዲሆኑ የማጽዳትና የማስዋብ ስራዎችም እየተከናወኑ እንደሚገኙም ጠቅሰዋል።

የዲላ ዩኒቨርስቲ ዕፅዋት ጥበቃና የኢኮ ቱሪዝም ማዕከል ዳይሬክተር ዶክተር ታሌሙ ሴታ በበኩላቸው ማዕከላቸው ብዝሃ ሕይወትን በመንከባከብ የአካባቢ ጥበቃ ስራዎችን እያከናወነ መሆኑን ገልጸዋል።

በተለይ በመጥፋት ላይ ያሉ አገር በቀል ዕጽዋቶችን ጨምሮ ከ500 በላይ የዕጽዋት ዝርያዎች በማዕከሉ ጥበቃና እንክብካቤ እየተደረገላቸው እንደሆነ ገልፀው ችግኞቹን አፍልቶ በነፃ የማሰራጨት ስራ እየተሰራ ነው ብለዋል።

በዚህም ዩኒቨርስቲው ብዝሃ ሕይወትን ከመጠበቅ ባለፈ ለተግባር ተኮር ትምህርት፣ ለምርምር እንዲሁም ለመዝናኛና ለተፈጥሮ ጥበቃ የድርሻውን እየተወጣ እንደሚገኝም ተናግረዋል።

 

 

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም