የመቻል ስፖርት ክለብን የቀድሞ ስምና ዝና ለመመለስ የመልሶ ማደራጀት ሥራ እየተሰራ መሆኑን የክለቡ የሥራ አመራር ቦርድ ገለፀ

አዲስ አበባ፤ ሰኔ 3/2016(ኢዜአ)፦  የመቻል ስፖርት ክለብን የቀድሞ ስምና ዝና ለመመለስ የመልሶ ማደራጀት ሥራ እየተሰራ መሆኑን የክለቡ የሥራ አመራር ቦርድ ገለፀ። 

የክለቡ 80ኛ ዓመት የምስረታ በዓል "መቻል ለኢትዮጵያ" በሚል መሪ ሀሳብ ከሰኔ 1-30/2016 ዓ.ም እንደሚከበርም ዛሬ ለመገናኛ ብዙሃን በሰጠው ጋዜጣዊ መግለጫ አስታውቋል ።

የመቻል ስፖርት ክለብ በ1936 ዓ.ም የተመሰረተ ሲሆን እግር ኳስና አትሌቲክስን ጨምሮ በልዩ ልዩ ስፖርቶች የተለያዩ ስመጥር ስፖርተኞችን አፍርቷል።

ክለቡ በነበረው ስምና ዝና አለመቀጠሉን የጠቀሰው ቦርዱ፥ ገናናነቱን ለመመለስ እቅዶች መነደፋቸውን ይፋ አድርጓል።

በጋዜጣዊ መግለጫው ላይ የተገኙት የመከላከያ ሠራዊት የሥነ-ልቦና ግንባታ ዋና ዳይሬክተር ሜጀር ጀነራል እንዳልካቸው ወልደኪዳን፤ የመቻል ስፖርት ክለብ የሀገር መከላከያ ሠራዊትን ይወክላል ብለዋል።

ስለሆነም ይህን የስፖርት ክለብ ለኅብረተሰቡ በደንብ በማስተዋወቅና ዓላማዎቹን በማስገንዘብ፤ በውጤት ማየት የራቀውን ደጋፊ መመለስ እንደሚያስፈልግ ገልፀዋል።

የክለቡ ፕሬዝዳንትና የቦርዱ ሰብሳቢ ዶክተር ሰይፈ ጌታሁን፤ ክለቡን በየጊዜው ከሚያጋጥመው የውጤት ማጣት በማላቀቅ፤ ለዋንጫ የሚፎካከር ክለብ ማድረግ ቅድሚያ የሚሰጠው ተግባር ነው ብለዋል።

የደጋፊ መሠረቱን ማጠናከርና ክለቡ የተደራጀ የገንዘብ አቅም እንዲኖረው ማስቻል ደግሞ፤ ሊሰራቸው ካቀዳቸው ተግባራት ዋና ዋናዎቹ መሆናቸውን ተናግረዋል።

ክለቡ የራሱ አካዳሚ፣ ስታዲየም፣ ሙዚየምና ዘመናዊ የስፖርተኞች ማረፊያ የማስገንባት ዕቅድ እንዳለው ገልፀዋል።

ለዚህም 80ኛ ዓመቱን ምስረታ በዓል እንደመልካም አጋጣሚ በመጠቀም ያቀዳቸውን ተግባራት ለመፈፀም እየሰራ መሆኑን ተናግረዋል።

ከዚህም ውስጥ የገቢ ማስገኛ ቴሌቶን የማሰባሰብ፣ የተለያዩ የስፖንሰርሺፕ ስምምነቶችን ማከናወን እንደሚገኙበት ገልፀዋል።

የመቻል የስፖርት ክለብ ከሰባት ወራት በፊት አዲስ ቦርድ አቋቁሞ ወደ ሥራ መግባቱ የሚታወስ ነው።

 

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም