ለሥነ-ሕዝብና ጤና ጥናት የመረጃ አሰባሰብ ሂደት መሳካት መገናኛ ብዙሃን የላቀ ሚናቸውን እንዲወጡ ተጠየቀ - ኢዜአ አማርኛ
ለሥነ-ሕዝብና ጤና ጥናት የመረጃ አሰባሰብ ሂደት መሳካት መገናኛ ብዙሃን የላቀ ሚናቸውን እንዲወጡ ተጠየቀ
አዲስ አበባ፤ ሰኔ 3/2016 (ኢዜአ)፦ ለአምስተኛው ዙር የኢትዮጵያ ሥነ-ሕዝብና ጤና ጥናት የመረጃ አሰባሰብ ሂደት መሳካት መገናኛ ብዙሃን የላቀ ሚናቸውን እንዲወጡ የኢትዮጵያ ስታትስቲክስ አገልግሎት ጠየቀ።
የኢትዮጵያ ስታትስቲክስ አገልግሎት ኢዜአን ጨምሮ ከተለያዩ የመገናኛ ብዙኃን ተቋማት ጋር በጋራ ለመሥራት የሚያስችል የመግባቢያ ሥምምነት ተፈራርሟል።
በዚሁ መርሃ ግብር ላይ ንግግር ያደረጉት የኢትዮጵያ ስታትስቲክስ አገልግሎት ዋና ዳይሬክተር በከር ሻሌ (ዶ/ር)፤ አምስተኛውን ዙር የኢትዮጵያ ሥነ-ሕዝብና ጤና ጥናት ለማካሄድ የቅድመ ዝግጅት ስራዎች በመከናወን ላይ መሆናቸውን ተናግረዋል።
በእስካሁኑ ሂደት ጥናቱን ለመጀመርም በመላ ሀገሪቷ 800 በላይ የናሙና መረጃ ማሰባሰቢያ ቦታዎች ስለመለየታቸው ጠቅሰዋል።
ለጥናቱ አስፈላጊ የሆኑ ቁሳቁሶችን ከማዘጋጀት በተጨማሪ መረጃ የሚያሰባስቡ ከ460 በላይ ባለሙያዎች ተለይተው ስልጠና በመውሰድ ላይ መሆናቸውንም ተናግረዋል።
በመሆኑም ለጥናቱ የመረጃ አሰባሰብ ሂደት መሳካት መገናኛ ብዙሃን የላቀ ሚናቸውን እንዲወጡ ዋና ዳይሬክተሩ ጠይቀዋል።
የኢትዮጵያ የስነ ህዝብና ጤና ጥናት በአምስት ዓመት አንድ ጊዜ የሚካሄድ ቢሆንም በተለያዩ ምክንያቶች መራዘሙ ይታወቃል።