ቀጥታ፡

 የኢትዮጵያን ክብርና ሉዓላዊነት የተሟላ ለማድረግ በተባበረ ክንድ ከተረጂነት መላቀቅ ይገባል  - ርዕሰ መስተዳድር አሻድሊ ሀሰን

አዲስ አበባ፤ ሰኔ 3/2016(ኢዜአ)፦ኢትዮጵያን ከተረጂት በማላቀቅ ክብሯን የተሟላ ለማድረግ ምርታማነትን በተባበረ ጥረት ማሳደግ  እንደሚጠይቅ  የቤኒሻንጉል ጉሙዝ ርዕሰ መስተዳድር አሻድሊ ሀሰን ገለጹ።

በማዕከላዊ ኢትዮጵያ ክልል ሆሳዕና ከተማ "ከተረጂነት ወደ ምርታማነት፤ ለተሟላ ሀገራዊ ሉዓላዊነትና ክብር"  በሚል መሪ ሀሳብ ህዝባዊ የውይይት መድረክ ተካሂዷል።

በመድረኩ የቤኒሻንጉል ጉሙዝ ርዕሰ መስተዳድር አሻድሊ ሀሰን፣ የብልፅግና ፓርቲ የህዝብና ዓለም አቀፍ ግንኙነት ኃላፊ አዲሱ አረጋ፣ የማዕከላዊ ኢትዮጵያ ክልል የመንግስት ዋና ተጠሪ ዶክተር ዲላሞ ኦቶሬ፣ ሌሎች ከፍተኛ አመራሮችና የተለያዩ የህብረተሰብ ክፍሎች ተገኝተዋል።

ርዕሰ መስተዳድር አሻድሊ በዚሁ ወቅት እንዳሉት፥ መንግስት ከለውጡ በፊት የነበሩና የተሻገሩ በርካታ እዳዎችን እየፈታ የሀገርን ስብራት እየጠገነ ነው።

ባለፉት ስድስት ዓመታት በስንዴ፣ በአረንጓዴ አሻራ፣ በሌማት ትሩፋት እንዲሁም በተለያዩ የልማት ስራዎች ላይ በተደረገው ርብርብ የኢትዮጵያን ስም በበጎ ያስጠሩ ውጤቶች መመዝገባቸውን ገልጸዋል።

ተረጂነትና አስተሳሰቡ አሁንም ፈተና መሆኑን ገልጸው፥ ክብርን የሚነካ እና ለጣልቃ ገብነት በር የሚከፍት በመሆኑ እንደ ሀገር የዕይታ ለውጥ የሚያመጣ ንቅናቄ መፍጠር አስፈልጓል ነው ያሉት።

በዚህም በኢትዮጵያ ያሉ ምቹ ሁኔታዎችን በመጠቀም ተረጂነትን ታሪክ ለማድረግ መንግስት ፖለቲካዊ ቁርጠኝነት በማሳየት የተግባር ምዕራፍ ውስጥ መግባቱንም ተናግረዋል።

በሁሉም መስክ የተገኙ ድሎችን ለማስቀጠል በተለይም የምግብ ሉዓላዊነትን ለማረጋገጥ ትጋትና ቅንጅት ወሳኝ እንደሆነም አስገንዝበዋል።

የማዕከላዊ ኢትዮጵያ ክልል የመንግስት ዋና ተጠሪ ዶክተር ዲላሞ ኦቶሬ በበኩላቸው፥ ልመና እና ተረጂነትን ማጥፋት የግልም የሀገርም የክብር ጉዳይ መሆኑን አስረድተዋል።


 

ክልሉ ለግብርና እና ሌሎችም ዘርፎች ምቹ ምህዳርና እምቅ ጸጋ እንዳለው ጠቅሰው፥ ይህንን ወደ ውጤት መቀየር የተናበበ ስራን እንደሚጠይቅ ጠቁመዋል።

ከተረጂነት መውጣት ብሔራዊ ጉዳይ በመሆኑ ሁሉም የሚጠበቅበትን ሚና እንዲወጣ ጥሪ አቅርበዋል።

የብልፅግና ፓርቲ የህዝብና ዓለም አቀፍ ግንኙነት ኃላፊ አዲሱ አረጋ፥ ኢትዮጵያ ከተረጂነት ለመላቀቅ የሚያስችሉ ጸጋዎች እንዳሏት ገልጸዋል።


 

ከተረጂነት መውጣት የሚቻለው በላብና ጠንካራ ጥረት መሆኑን ጠቅሰው፥ የዕይታ ለውጥ በማምጣት ጸጋዎችን ወደ ጥቅም መቀየር እንደሚገባም ጠቁመዋል።

የውይይቱ ተሳታፊዎች ተረጂነት ለማጥፋት ስንፍናን ማስወገድ  እንደሚገባ ገልጸው፥ በምግብ ራስን ለመቻል የተጀመሩ ሀገራዊ የልማት ውጥኖችን ለማሳካት በግንባር ቀደምትነት እንደሚሰሩ ተናግረዋል።

ምርታማነትን ማሳደግ ከተረጅነት መውጫ አንዱ መንገድ በመሆኑ ለስኬቱ ቁርጠኛ ነን ብለዋል።

 
 

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም