የኢትዮጵያ አየር መንገድ አስተማማኝና ተደራሽ የሆነ የአየር ትራንስፖርት አገልግሎት ለመስጠት እየተጋ ነው - አቶ መስፍን ጣሰው - ኢዜአ አማርኛ
የኢትዮጵያ አየር መንገድ አስተማማኝና ተደራሽ የሆነ የአየር ትራንስፖርት አገልግሎት ለመስጠት እየተጋ ነው - አቶ መስፍን ጣሰው
አዲስ አበባ፤ ሰኔ 3/2016(ኢዜአ)፦የኢትዮጵያ አየር መንገድ አስተማማኝና ተደራሽ የሆነ የአየር ትራንስፖርት አገልግሎት ለመስጠት እየተጋ መሆኑን የተቋሙ ዋና ሥራ አስፈጻሚ መስፍን ጣሰው ገለጹ።
የኢትዮጵያ አየር መንገድ ዛሬ ማለዳ በቦትስዋና የቱሪስት መዳረሻ ወደ ሆነችው ማኡን ከተማ በረራ ጀምሯል።
በረራውም በሳምንት ሦስት ጊዜ የሚደረግ መሆኑ ታውቋል።
በማስጀመሪያው መርኃ-ግብሩ የኢትዮጵያ አየር መንገድ ግሩፕ ዋና ሥራ አስፈጻሚ መስፍን ጣሰው፤ የአየር መንገዱ የንግድ ዘርፍ ዋና ኃላፊ ለማ ያዴቻ በኢትዮጵያ የቦትስዋና አምባሳደር ተብሌሎ አልፈርድ ቦአንግ ተገኝተዋል።
የኢትዮጵያ አየር መንገድ ግሩፕ ዋና ሥራ አስፈጻሚ መስፍን ጣሰው በዚሁ ጊዜ እንደገለጹት፤ አየር መንገዱ በስትራቴጂክ ዕቅዱ መሠረት ዓለም አቀፍና አህጉራዊ መዳረሻውን በየጊዜው እያሰፋ ይገኛል።
አየር መንገዱ በተለይ አፍሪካን ከአፍሪካውያንና ከተቀረው ዓለም ጋር ለማስተሳሰር የጀመረውን ሥራ አጠናክሮ መቀጠሉንም ነው ዋና ሥራ አስፈጻሚው የገለጹት።
በዚህም በአየር ትራንስፖርት አፍሪካን በማስተሳሰር ለአፍሪካ ነፃ የንግድ ቀጣና መፋጠን የበኩሉን ድርሻ እየተወጣ ይገኛል ብለዋል።
አየር መንገዱ በረራ የጀመረባት ማኡን ከተማ በአፍሪካ 65ኛ መዳረሻው መሆኑን ገልፀዋል።
አየር መንገዱ ከስምንት ዓመታት በፊት ጀምሮ ወደ ቦትስዋና ዋና ከተማ ጋቦሮኒ በረራ የሚያደርግ መሆኑን በማስታወስ የማኡን ከተማ በቦትስዋና ሁለተኛዋ መዳረሻ መሆኗን ጠቁመዋል።
በመሆኑም የኢትዮጵያ አየር መንገድ አፍሪካ ውስጥ አስተማማኝና ተደራሽ የሆነ የአየር ትራንስፖርት አገልግሎት ለመስጠት እየተጋ መሆኑን ነው የገለጹት።
የቦትስዋና አምባሳደር ተብሌሎ አልፈርድ ቦአንግ በበኩላቸው፤ የበረራው መጀመር ሁለቱ አገራት ያላቸውን የኢኮኖሚ ዲፕሎማሲና የሕዝብ ለሕዝብ ትስስር ለማጠናከር ከፍተኛ ሚና እንደሚኖረው ገልፀዋል።
በተለይ ማኡን ከተማም የቱሪዝም መዳረሻ መሆኗን በመጥቀስ የቱሪዝም ፍሰትን ለማሳደግ ትልቅ አቅም እንደሚሆን ተናግረዋል።
የኢትዮጵያ አየር መንገድ አፍሪካን ከአፍሪካውያንና ከተቀረው ዓለም ለማስተሳሰር እየሄደበት ያለው ርቀትም የሚያስደንቅ ነው ብለዋል።
የኢትዮጵያ አየር መንገድ ባሉት 147 የሚጠጉ አውሮፕላኖች 136 ዓለም አቀፍና 22 የአገር ውስጥ መዳረሻዎችን እየሸፈነ ይገኛል።