በሀረር ከተማ እድሜዋን የሚመጥን እድገትን እውን ለማድረግ በትኩረት እየተሰራ ነው- አቶ ኦርዲን በድሪ

አዲስ አበባ፤ ሰኔ 3/2016(ኢዜአ)፦ በሀረር ከተማ እድሜዋን የሚመጥን እድገት እውን ለማድረግ በትኩረት እየተሰራ መሆኑን የሀረሪ ክልል ርዕሰ መስተዳድር አቶ ኦርዲን በድሪ ተናገሩ።

ርዕሰ መስተዳድሩ የሀረር ከተማን ስትራቴጂክ የልማት እቅድ ለመምራት ከተቋቋመው ግብረሃይል ጋር ተወያይተዋል።

በመድረኩም በከተማው እየተከናወኑ የሚገኙ ዘርፈ ብዙ ስራዎች ላይ ምክክር ተደርጓል።

በዚህ ወቅትም ርዕሰ መስተዳድሩ አቶ ኦርዲን በድሪ በተለይም በአሁኑ ወቅት ሀረር ከተማን የሚመጥናት እድገት እውን ለማድረግ በልዩ ሁኔታ ርብርብ እየተደረገ ነው ብለዋል ።

ከዚህ ቀደም በከተማዋ ሲሰሩ የቆዩ ስራዎች በቅንጅት አለመሰራቱ በውጤታማነት ላይ ተፅዕኖ አሳድሮ መቆየቱን ጠቅሰው፤ አሁን ላይ እየተከናወኑ የሚገኙ ዘርፈ ብዙ የልማት ስራዎችን በቅንጅት አጠናክሮ ማስቀጠል እንደሚገባ ተናግረዋል።


 

በተለይ በከተማዋ እየተሰሩ የሚገኙ የመሠረተ ልማት ስራዎች፣ መሬትን በፕላን መምራት፣ የግንባታ ፍቃድ እና ቁጥጥር ስራዎችን አጠናክሮ ማስቀጠል አስፈላጊ መሆኑን አመላክተዋል።

ሀረር ከተማን ውብ፣ ጽዱ እንዲሁም ለነዋሪው እና ለጎብኚው ምቹ ለማድረግ እየተከናወኑ የሚገኘውን አበረታች ስራዎችን ማጎልበት ይገባል ብለዋል።

በሌላ በኩል በከተማዋ ጽዳትና ውበት ላይ ተፅዕኖ እያሳደረ የሚገኘው የውጪ ማስታወቂያ በአፋጣኝ ልጓም ሊበጅላቸው እንደሚገባ ነው ያሳሰቡት።


 

በየተቋሙ ተጀመረው ያልተጠናቀቁ የመሰረተ ልማት ዝርጋታዎችን በቀሪ የአንድ ወር ጊዜ ውስጥ ማጠናቀቅ እንደሚገባ አቅጣጫ አስቀምጠዋል።

ህገ ወጥ የጎዳና ንግድና አገልግሎት ስርአት ለማስያዝ የተጀመሩ ስራዎችን አጠናክሮ ማስቀጠል እንደሚገባ መናገራቸውን የክልሉ ኮሙኒኬሽን ጉዳዮች ጽህፈት ቤት መረጃ ያመለክታል።

የክልሉ ከተማ ልማትና ኮንስትራክሽን ቢሮ፣ የሀረር ከተማ ማዘጋጃ ቤት፣ የባህል ቅርስና ቱሪዝም ቢሮ ፣ ውሃና ፍሳሽ ባለስልጣን፣ የክልሉ መንገድ ልማት እና ትራንስፖርት ቢሮ የኢትዮጵያ ኤሌክትሪክ አገልግሎት ሀረር ቅርንጫፍ ፅህፈት ቤትን ጨምሮ የምስራቅ ሪጅን ኢትዮ ቴሌኮምን ያካተተ ግብረሀይል ተቋቋሞ ወደ ስራ መግባቱ ይታወሳል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም