ቀጥታ፡

የኢትዮጵያ ስታትስቲክስ አገልግሎት ከተለያዩ የመገናኛ ብዙኃን ተቋማት ጋር በጋራ ለመሥራት ሥምምነት ተፈራረመ

አዲስ አበባ፤ ሰኔ 3/2016(ኢዜአ)፦ የኢትዮጵያ ስታትስቲክስ አገልግሎት ከተለያዩ የመገናኛ ብዙኃን ተቋማት ጋር በጋራ ለመሥራት የሚያስችለውን የመግባቢያ ሥምምነት ተፈራረመ።

ሥምምነቱን የተቋሙ ሥራ አመራር ዋና ሥራ አስፈጻሚ አቶ ኤቢሳ አሰፋ ከተለያዩ የመገናኛ ብዙኃን ተቋማት ተወካዮች ጋር ተፈራርመዋል። 

ሥምምነቱ ተቋሙ ለአምስተኛ ጊዜ በሀገሪቱ  የሚያካሂደው የኢትዮጵያ ሥነ-ሕዝብና ጤና ጥናት ውጤታማ እንዲሆን ያስችላል ተብሏል።

የኢትዮጵያ ስታትስቲክስ አገልግሎት ዋና ዳይሬክተር በከር ሻሌ (ዶ/ር) በዚሁ ጊዜ እንደገለጹት፤ 5ኛው ዙር የኢትዮጵያ ሥነ-ሕዝብና ጤና ጥናት ለማካሄድ የተለያዩ ተግባራት እየተከናወኑ ነው። 


 

እየተሰሩ ካሉ ሥራዎች መካከል በተለያዩ የሀገሪቱ አካባቢዎች ተዘዋውረው መረጃ ለሚሰበስቡ አካላቶች ሥልጠና የመስጠት ሥራ በመሠራት ላይ መሆኑን ተናግረዋል።

የሥነ-ሕዝብና ጤና ጥናት ውጤታማ እንዲሆን መገናኛ ብዙኃን ለማኅበረሰቡ ግንዛቤ በማስጨበጥ ተጨባጭ መረጃ እንዲሰበሰብ ማድረግ አለባቸው ነው ያሉት።  

ለዚህም ዛሬ ከመገናኛ ብዙኃን ተቋማት ጋር ሥምምነት ላይ መደረሱን ጠቁመዋል።  

ከተለያዩ የመገናኛ ብዙኃን ተቋማት ጋር የተደረሰው ሥምምነት በጥናቱ ዙሪያ አስፈላጊ የሆኑ መረጃዎችን በተለያዩ ቋንቋዎች ተደራሽ ለማድረግም ያግዛል ብለዋል።

 

 

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም