በሆሳዕና ከተማ እየተከናወኑ ያሉ የልማት ሥራዎች ተጨባጭ ውጤት እየተመዘገበባቸው ነው - ዲላሞ ኦቶሬ (ዶ/ር) - ኢዜአ አማርኛ
በሆሳዕና ከተማ እየተከናወኑ ያሉ የልማት ሥራዎች ተጨባጭ ውጤት እየተመዘገበባቸው ነው - ዲላሞ ኦቶሬ (ዶ/ር)

አዲስ አበባ፤ ሰኔ 3/2016(ኢዜአ)፦በሆሳዕና ከተማ በነዋሪው ትብብር እየተከናወኑ ያሉ የልማት ሥራዎች ተጨባጭ ውጤት እየተመዘገበባቸው መሆኑን የማዕከላዊ ኢትዮጵያ ክልል የመንግሥት ዋና ተጠሪና የክልሉ የብልጽግና ፓርቲ ጽህፈት ቤት ኃላፊ ዲላሞ ኦቶሬ (ዶ/ር )ገለጹ።
የፌዴራል እና የክልል ከፍተኛ የሥራ ኃላፊዎች በማዕከላዊ ኢትዮጵያ ክልል ሆሳዕና ከተማ እየተከናወኑ ያሉ የልማት ሥራዎችን ተዘዋውረው ጎብኝተዋል።
የቤንሻንጉል ጉሙዝ ክልል ርዕሰ መስተዳድር አሻድሊ ሐሰን፣ የብልፅግና ፓርቲ የሕዝብና ዓለም አቀፍ ግንኙነት ኃላፊ አዲሱ አረጋ፣ የማዕከላዊ ኢትዮጵያ ክልል የመንግሥት ዋና ተጠሪ ዲላሞ ኦቶሬ (ዶ/ር) እና ሌሎች አመራሮች በጉብኝቱ ላይ ተሳትፈዋል።
የማዕከላዊ ኢትዮጵያ ክልል የመንግሥት ዋና ተጠሪ እና የክልሉ የብልጽግና ፓርቲ ጽህፈት ቤት ኃላፊ ዲላሞ ኦቶሬ (ዶ/ር) በዚሁ ወቅት እንዳሉት፤ ጉብኝቱ ትልቅ ትርጉም የሚሰጠው መሆኑን ገልፀዋል።
በሁሉም የልማት መስኮች ሕብረተሰቡን ማሳተፍ ከተቻለ በአጭር ጊዜ ውስጥ ለውጥ ማስመዝገብ እንደሚቻል ተናግረዋል።
አሁን ያለው ትውልድ የልማት አርበኛ በመሆን ታሪክ ሰርቶ ለመጪው ትውልድ ሊያስተላልፍ ይገባል ብለዋል።
በሆሳዕና ከተማ እየተከናወኑ ያሉ የልማት ሥራዎች በተጨባጭ በኅብረተሰቡ ላይ ለውጥ እያመጡ መሆናቸውን ገልፀዋል።
ለአብነትም በጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ (ዶ/ር) ሀሳብ አመንጪነት የተጀመሩ የሌማት ትሩፋት ሥራዎች ከራስ አልፈው ከተማንና ማኅበረሰብን እየቀየሩ እንደሚገኙ ተናግረዋል።
እንዲሁም በማኅበራዊ አገልግሎቶች የሚሰሩ መሠረተ-ልማቶች ሕብረተሰቡን ባሳተፈ መንገድ እየተከናወኑ መሆኑን ጠቅሰዋል።
እየተከናወኑ ባሉ የልማት ሥራዎች ተፎካካሪ ፓርቲዎች ጭምር ተቀናጅተው የሀገር ግንባታ እንዲሁም ድህነት ቅነሳ ላይ በጋራ እየተሰራ መሆኑን ተናግረዋል።
ሆሳዕና የሰላም ተምሳሌት ከተማ መሆኗን ገልጸው፤ ሕብረተሰቡም በልማት ሥራ ደጀንነቱን እያስመሰከረ መሆኑን ጠቁመዋል።
ሌሎች አካባቢዎችም ከመንግሥት ጎን በመቆም ለልማት በጋራ መሥራት እንዳለባቸው አመላክተዋል።
የሀዲያ ዞን አስተዳዳሪ ማቴዎስ አኒዮ በበኩላቸው፤ በሆሳዕና ከተማ እየተከናወኑ ያሉ የሌማት ትሩፋት፣ የከተማ ግብርና እና የማኅበራዊ አገልግሎት መሠረተ-ልማት ግንባታ ሥራዎች ተሞክሮ የሚወሰድባቸው መሆኑን ተናግረዋል።
እነዚህ ሥራዎች ማህበረሰቡን በቀጥታ ተጠቃሚ የሚያደርጉ መሆናቸውን ገልጸው፤ ቀጣይነት ባለው መልኩ የከተማውን ነዋሪ ተጠቃሚ የሚያደርጉ ሥራዎች ተጠናክረው እንደሚቀጥሉ ጠቁመዋል።
በነዋሪው ዘንድ በርካታ የልማት ጥያቄዎች መኖራቸውን ገልጸው፤ ይህን ለመመለስ ህዝቡን በማስተባበር መንግሥት ኃብት በመመደብ እና ጉልበትን በማቀናጀት እንደሚሰራ ተናግረዋል።