ቀጥታ፡

አሽከርካሪዎችና እግረኞች የትራፊክ ህግና ደንብን ከማክበር ሊዘናጉ አይገባም

አዲስ አበባ ፤ሰኔ 3/2016(ኢዜአ)፦አሽከርካሪዎችና እግረኞች በእለት ተዕለት ህይወታቸው የትራፊክ ህግና ደንብን ከማክበር  ሊዘናጉ እንደማይገባ በአዲስ አበባ ፖሊስ ትራፊክ ቁጥጥር መምሪያ  አስታወቀ።

የአዲስ አበባ ፖሊስ ትራፊክ ቁጥጥር መምሪያ 10ኛውን ወርሃዊ የትራፊክ ህግ ግንዛቤ ማስጨበጫ ፕሮግራም አካሒዷል፡፡


 

ፕሮግራሙ የተካሔደው በመስቀል አደባባይ ሲሆን የትራፊክ ፖሊስ አባላት እና በትራፊክ አደጋ ላይ የሚሰሩ በጎ ፈቃደኞች ተገኝተዋል።

በአዲስ አበባ ፖሊስ ትራፊክ ቁጥጥር መምሪያ የሞተር አጀብና ቁጥጥር ምክትል ዳይሬክተር ዋና ኢንስፔክተር ሰላሙ ካልፒሶ  እንዳሉት፤ የፕሮግራሙ አላማ እግረኞችና አሽከርካሪዎች የትራፊክ ህግን አክብረው እንዲንቀሳቀሱ በማድረግ በሰውና በንብረት ላይ የሚደርሱ ጉዳቶችን መቀነስ ነው።

ለትራፊክ አደጋ ከሚያጋልጡ ጉዳዮች መካከል ከፍጥነት በላይ ማሽከርከር፣ ስልክ መነካካት፣ የደህንነት ቀበቶ አለማድረግና መስመርን ጠብቆ አለመንቀሳቀስ ይገኙበታል ብለዋል፡፡

በመሆኑም በሰውና በንብረት ላይ የሚደርሰውን አደጋ ለመቀነስ አሽከርካሪዎች እና እግረኞች የትራፊክ ህግ እና ደንብን አክብረው መጓዝ እንደሚጠበቅባቸው አስገንዝበዋል፡፡

 

 

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም