በሆሳዕና ከተማ ሕዝባዊ የውይይት መድረክ እየተካሄደ ነው - ኢዜአ አማርኛ
በሆሳዕና ከተማ ሕዝባዊ የውይይት መድረክ እየተካሄደ ነው

አዲስ አበባ፤ ሰኔ 3/2016(ኢዜአ)፦ በማዕከላዊ ኢትዮጵያ ክልል ሆሳዕና ከተማ "ከተረጂነት ወደ ምርታማነት፤ ለተሟላ ሀገራዊ ሉዓላዊነትና ክብር" በሚል መሪ ሐሳብ ሕዝባዊ የውይይት መድረክ እየተካሄደ ነው።
በመድረኩ የቤኒሻንጉል ጉሙዝ ክልል ርዕሰ መስተዳድር አሻድሊ ሀሰን፣ የብልፅግና ፓርቲ የሕዝብና ዓለም አቀፍ ግንኙነት ኃላፊ አዲሱ አረጋ፣ የማዕከላዊ ኢትዮጵያ ክልል የመንግሥት ዋና ተጠሪ ዲላሞ ኦቶሬ(ዶ/ር) እና ሌሎች አመራሮች ተገኝተዋል።
ከገጠርና ከከተማ ወረዳዎች የተውጣጡ የተለያዩ የኅብረተሰብ ክፍሎች በሕዝባዊ ውይይቱ እየተሳተፉ ነው።
የቤኒሻንጉል ጉሙዝ ክልል ርዕሰ መስተዳድር አሻድሊ ሐሰን በዚሁ ወቅት እንዳሉት፤ የለውጡ መንግሥት ለተረከባቸው ዕዳዎች መፍትሔ በመስጠትና ስብራቶችን በመጠገን የብልጽግና ጉዞውን ጀምሯል።
ባለፉት ስድስት ዓመታት በስንዴ፣ በአረንጓዴ አሻራ፣ በሌማት ትሩፋት እንዲሁም በተለያዩ የልማት ሥራዎች ላይ ርብርብ በማድረግ ስብራቶችን እየጠገነ መሆኑን ገልፀዋል።
የተወረሱ ዕዳዎችን ወደ ምንዳ በመቀየር ለመጪው ትውልድ የበለጸገች ሀገር ለማስተላለፍ አበክሮ እየሰራ መሆኑንም ተናግረዋል።
የተገኙ ድሎችን በማስቀጠል ተረጂነትን በማጥፋት የምግብ ሉዓላዊነትን ለማረጋገጥ የሁሉንም ትብብር እንደሚጠይቅም አክለዋል።
የብልፅግና ፓርቲ የሕዝብና ዓለም አቀፍ ግንኙነት ኃላፊ አዲሱ አረጋ በበኩላቸው ከተረጂነት መውጣት የሉዓላዊነት ጉዳይ መሆኑን ተናግረዋል።
ለዚህም በመንግሥት የተጀመሩ ኢኒሼቲቮች ላይ ርብርብ በማድረግ ትውልዱ ከድህነት በመላቀቅ የዘመኑን አድዋ መድገም እንደሚገባው አመላክተዋል።
የሀዲያ ዞን አስተዳዳሪ ማቴዎስ አኒዮ ምርታማነትን ለማረጋገጥ ተባብሮ መሥራት እንደሚገባ አስገንዝበዋል።
ከልመናና ከተረጂነት አዙሪት ለመውጣት እየተሰሩ ያሉ ሥራዎች ውጤት እያፈሩ መሆናቸውን ገልፀዋል።
ከራስ አልፎ ለሌሎች የምንተርፍ እንድንሆን ጠንካራ የሥራ ባህል መፍጠር እንደሚገባና ከተመጽዋችነት በመላቀቅ ለምርታማነት ርብርብ ማድረግ ይገባል ብለዋል።