ቀጥታ፡

በአዲስ አበባ እውቀትና ክህሎት መር የሕግ አስከባሪ ተቋማት ግንባታ ተጠናክሮ ይቀጥላል

አዲስ አበባ፤ ሰኔ 2/2016(ኢዜአ)፦ ከኢትዮጵያ አልፎ የዓለም አቀፍ ዲፕሎማሲ ማዕከል የሆነችው አዲስ አበባ በእውቀትና ክህሎት ብቁ የሆኑ ዘመናዊ የሕግና ደንብ አስከባሪ ተቋማት እንዲኖራት በትኩረት እየተሰራ መሆኑን የከተማ አስተዳደሩ ሰላም እና ፀጥታ ቢሮ ኃላፊዋ ሊድያ ግርማ ገለጹ።

የአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር በኢትዮጵያ ፖሊስ ዩኒቨርሲቲ በ5ኛ ዙር ወታደራዊ የተግባርና ንድፈ-ሃሳብ ስልጠና ሲከታተሉ የቆዩ የደንብ ማስከበር አመራርና ኦፊሰር አባላትን አስመርቋል። 


 

በምርቃት ሥነ-ስርዓቱ በአዲስ አበባ ከተማ ምክር ቤት የሰላም፣ ፍትሕና መልካም አስተዳደር ጉዳዮች ቋሚ ኮሚቴ ሰብሳቢ ሙሉነህ ደሳለኝ፣ የፌደራል ፖሊስ መኮንኖች እና ጥሪ የተደረገላቸው አካላት ተገኝተዋል።  

የአዲስ አበባ ሰላምና ፀጥታ አስተዳደር ቢሮ ኃላፊዋ ሊዲያ፤ ምሩቃኑ የመዲናዋን ነዋሪዎች በታላቅ ሙያዊ የስነ-ምግባር ኃላፊነት ሊያገለግሉ እንደሚገባ አሳስበዋል።

ለደንብ ማስከበር አመራርና ኦፊሰር አባላት የሚሰጠው ስልጠናም የሕግ መተላለፍና ሕገ-ወጥነትን በመቆጣጠር የከተማዋን ሰላምና ደኅንነት ለማስቀጠል አይነተኛ ሚና እንዳለው ተናግረዋል።

የደንብ ማስከበር ባለስልጣን የመሬት ወረራ፣ የደንብ መተላለፍ፣ የሕግ ጥሰትና ብልሹ አሰራሮችን መቆጣጠር የሚያስችል አመራርና ኦፊሰር አባላትን ለማፍራት ለሰጠው ትኩረት ምስጋና አቅርበዋል።

የኢትዮጵያ መዲና የዓለም ዲፕሎማሲ ማዕከል የሆነችው አዲስ አበባ በእውቀትና ክህሎት የታነጸ ዘመናዊ የሕግና ደንብ አስከባሪ ተቋማት እንዲኖራት በትኩረት እየተሰራ ነው ብለዋል።

የኢትዮጵያ ፖሊስ ዩኒቨርሲቲ ፕሬዚዳንት ምክትል ኮሚሽነር ጄኔራል መስፍን አበበ፤ ምሩቃኑ የሚሰጣቸውን ኃላፊነት በብቃት መወጣት የሚያስችል የአካል ብቃትና የንድፈሃሳብ ስልጠና መውሰዳቸውን ገልጸዋል።


 

በመዲናዋ በጥናትና ምርምር የተመሰረተ የማህበረሰብ አገልግሎት መስጠት እንዲቻል በተለያዩ ዙሮች ለበርካታ የደንብ ማስከበር አመራርና ኦፊሰር አባላት ስልጠና መሰጠቱን አስታውቀዋል።

የአዲስ አበባ ደንብ ማስከበር ባለስልጣን ሥራ አስኪያጅ ሻለቃ ዘሪሁን ተፈራ፤ ባለስልጣኑ የደንብ መተላለፍና ህገ-ወጥነትን የማስተካከል፣ መቆጣጠርና እርምጃ የመውሰድ ኃላፊነቱን እየተወጣ ነው ብለዋል።


 

የደንብ ማስከበር አመራርና ኦፊሰር አባላት ሌብነትና ብልሹ አሰራርን በዕውቀት፣ ክህሎት፣ በአካል ብቃትና ንድፈ ሃሳብ መከላከል በሚያስችል መልኩ ስልጠናቸውን ማጠናቀቃቸውን ገልጸዋል።

ተመራቂ የደንብ ማስከበር አመራርና ኦፊሰር አባላት በበኩላቸው፥ በመዲናዋ የደንብ መተላለፍና ህገ-ወጥነት መቆጣጠር የሚያስችል እውቀትና ክህሎት  ከስልጠናው ማግኘታቸውን ተናግረዋል።

የወሰዱት የአካል ብቃትና የንድፈ ሃሳብ ስልጠናም የመዲናዋን ነዋሪዎች በሙያዊ ስነ-ምግባር ለማገልገል ትልቅ አቅም እንደሚሆናቸው ጠቁመዋል። 

በምርቃት ሥነ-ስርዓቱ በስልጠናው የላቀ ውጤት ላስመዘገቡ የደንብ ማስከበር አመራርና ኦፊሰር አባላት ሽልማትና ዕውቅና ተሰጥቷል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም