ቀጥታ፡

ወጣቶች የዕኩይ ቡድኖችን እንቅስቃሴ ለማክሸፍና ልማትን ለማረጋገጥ ሚናቸው የጎላ መሆኑ ተገለጸ

አዲስ አበባ፤ ሰኔ 2/2016(ኢዜአ)፦ በየአካባቢው የጸጥታ ችግርና በህዝብ ላይ ውዥንብር ለመፍጠር የሚሞክሩ ዕኩይ ቡድኖችን እንቅስቃሴ በማክሸፍ ረገድ የወጣቶች ሚና የጎላ መሆኑን የቢሾፍቱ ከተማ አስተዳደር ከንቲባ አለማየሁ አሰፋ ገለጹ፡፡

የቢሾፍቱ ከተማ አስተዳደር ከወጣት ለሰላምና ልማት ማህበር ጋር በመተባበር ወጣቶች በሀገራቸው ሰላምና ልማት ላይ የሚኖራቸውን ተሳትፎ ማጎልበት የሚያስችል ስልጠና ሰጥቷል፡፡


 

የወጣት ለሰላምና ለልማት ማህበር ኦሮሚያን ጨምሮ በተለያዩ ክልሎች የወጣቶችን ስብዕና ለመገንባት በሥራ ፈጠራና አቅም ግንባታ ዙሪያ ሥልጠና የሚሰጥ መንግስታዊ ያልሆነ ድርጅት ነው፡፡

የቢሾፍቱ ከተማ አስተዳደር ከንቲባ አለማየሁ አሰፋ ለኢዜአ እንዳሉት፤ ወጣቶች የነገ ሀገር ተረካቢዎች በመሆናቸው ሰላምና ጸጥታ በማስጠበቅ በኩል ሚናቸው ከፍ ያለ ነው፡፡

የወጣቶች የነቃ ተሳትፎ የራሳቸውንና ህዝቡን ተጠቃሚነት ለማረጋገጥ፤ ብሎም ለሀገር ሁለንተናዊ ስኬት መሰረት መሆኑንም ገልጸዋል፡፡

በመሆኑም መንግስት ያመቻቸላቸውን ምቹ ሁኔታ በመጠቀም ሀብት ማፍራት፣ በሰላማዊ ውይይት ችግሮችን በመፍታት እና የተዛቡ ትርክቶችን በማረቅ አርዓያ መሆን አለባቸው ነው ያሉት፡፡

የቢሾፍቱ ከተማ ወጣቶች በሰላምና ልማት ላይ በሚደረገው ምክክር የነቃ ተሳትፎ የሚያደርጉበት መድረክ መዘጋጀቱንም ገልጸዋል፡፡

በዚህም ወጣቶች ጥያቄያቸውን በኃይል ሳይሆን በሰላማዊና በውይይት መፍታት እንደሚችሉ መግባባት በመፍጠር ተከታታይ ውይይቶች እየተደረጉ መሆኑንም ጠቅሰዋል፡፡

በኦሮሚያ ክልል በተወሰኑ አካባቢዎች የሸኔ ሽብር ቡድን እንቅስቃሴን በማክሰምና ሰላምን በማስጠበቅ ረገድ የወጣቶች ተሳትፎ ወሳኝ እንደሆነም ገልጸዋል።

በተለይም በተሳሳተ መንገድ ወደ ሽብር ቡድኑ የገቡ ወጣቶች መንግስት ያመቻቸውን የሰላም ጥሪ በመጠቀም በይቅርታ ወደ ማህበረሰቡ እንዲቀላቀሉ እየተሰራ መሆኑን ጠቁመዋል።

ከዚህም ባለፈ ዕኩይ ዓላማቸውን ለማሳካት በህዝቡ መካከል ውዥንብር ለመፍጠር የሚሞክሩ አካላትን ድርጊት በማክሸፍ ረገድ ወጣቶች ጉልህ ሚና እያበረከቱ ነው ብለዋል፡፡


 

የወጣት ለሰላምና ልማት ማህበር ፕሬዝዳንት ቦና ደበላ፤ ወጣቶች በተሰማሩበት ቦታ ሁሉ ንቁ ተሳትፎ ማድረግ እንዳለባቸው ጠቅሰዋል፡፡

በኢትዮጵያ ዘላቂ ሰላም ለማስፈንና ልማትን ለማረጋገጥ የወጣቶች ድርሻ ከፍተኛ መሆኑን ገለጸው፤ ወጣቶች በአስተሳሰብና በተግባር አንድነት ካልተቀየሩ ለውጥ ማምጣት እንደማይቻልም ነው የተናገሩት፡፡

ከዚህ አኳያ እንደ ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ (ዶ/ር)፣ ቢኒያም በለጠ፣ ማርቲን ሉተር ኪንግና ቢል ጌት ካሉ ባለ ራዕይ ግለሰቦች መማር እንደሚገባቸውም ጠቁመዋል፡፡

በኢትዮጵያ ሰፊ የስራ አማራጮች መኖራቸውን ገልጸው፤ እነዚህን እድሎች በአግባቡ ለመጠቀም መንግስት በቅድሚያ ለወጣቶች በቂ ክህሎትና ግንዛቤ እንዲፈጥር ጠይቀዋል፡፡

መንግስት በሚፈጥራቸው ምቹ ሁኔታዎች ለመጠቀም ደግሞ ወጣቶች ራሳቸውን ለስልጠና እና ለስራ በማዘጋጀት እና ባለድርሻ አካላትም ትብብራቸውን በማጎልበት ሀገርን ማሳደግ አስፈላጊ ነው ብለዋል።

የቢሾፍቱ ከተማ ነዋሪዎች በበኩላቸው፤ ከመንግስት ጋር በመቀራረብ ለሀገር ሰላምና ልማት እየሰሩ መሆኑን ገልጸዋል፡፡

ለኢዜአ አስተያየት የሰጡት ሽመልስ ኢንሰርሙ፣ ሻምበል ደቻሳ እና ተሬቻ ሆርዶፋ ሀገራዊ መግባባትና ልማትን ማምጣት በሚችሉ ጉዳዮች በንቃት እንደሚሳተፉ አንስተዋል፡፡

ወጣቶች የሀገር ኢኮኖሚና የሰላም የጀርባ አጥንት መሆናቸውን ገልጸው፤ ልዩነቶችና አለመግባባቶች የሚፈቱት በውይይት ብቻ እንደሆነም ተናግረዋል፡፡

በመሆኑም የሰላምና የልማት ጥያቄዎቻችን በሰላማዊ መንገድ እልባት እንዲያገኙ ከመንግስት ጎን እንሰራለን ነው ያሉት፡፡

መንግስትም የወጣቶችን ጥያቄ በጽሞና በማዳመጥ ማወያየትና አቅማቸውን ለማሳደግ ተገቢውን ስልጠና መስጠት እንዳለበት ገልጸዋል፡፡

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም