ቀጥታ፡

በክልሉ ያሉ ባዶ መሬቶችን በማልማት ለመጪው ትውልድ ምንዳን ማውረስ ይገባል - ዶክተር ኤርጎጌ ተስፋዬ

ሐረር ፤ሰኔ 02/2016 (ኢዜአ)፦በክልሉ ያሉ ባዶ መሬቶችን በማልማት ለመጪው ትውልድ ምንዳን ማውረስ ይገባል ሲሉ የሴቶችና ማህበራዊ ጉዳይ ሚኒስትር ዶክተር ኤርጎጌ ተስፋዬ ገለጹ።

ሚኒስትሯ ይህን የገለጹት "ከተረጂነት ወደ ምርታማነት ለተሟላ ሀገራዊ ሉዓላዊነትና ክብር" በሚል መሪ ሐሳብ በሐረር በተካሄደው የውይይት መድረክ ላይ ነው።


 

ዶክተር ኤርጎጌ እንዳሉት ሰፊ መሬት፣ በቂ ውሃና ተስማሚ አየር ንብረት እያለን ተረጂነትን ተሸክመን መቀጠል የለብንም።

በመሆኑም የሐረሪ ክልል ህዝብ በክልሉ ያሉ ባዶ መሬቶችን በማልማት ለመጪው ትውልድ ምንዳን ማውረስ ይገባዋል።

"በእርዳታ ያደገ አገር የለም" ያሉት ሚኒስትሯ፤ የስራ ባህልን በመቀየር ከተረጂነት ለመውጣት የሚያስችሉ እድሎችን አሟጦ በመጠቀም ምርታማነትን ማሳደግ እንደሚገባ አስገንዝበዋል።

በመድረኩ ላይ የተገኙት የጋምቤላ ክልል ምክትል ርዕሰ መስተዳድር አቶ ታንኳይ ጆክ የክልሉ ነዋሪና አርሶ አደሩ ምርትና ምርታማነትን ለማጎልበት በተለያዩ ዘርፎች የጀመሩት ስራ አበረታች ነው ብለዋል።

በተለይ የክልሉ መንግስት ባዶ መሬት ፆም እንዳያድር የጀመረው ስራ የሚበረታታ መሆኑን ጠቅሰው ከኤሌትሪክ መቆራረጥ፣ ከምርት ግብዓት እጥረት፣ ከገበያ ትስስርና ከሌሎች ጋር የሚታዩ ክፍተቶችን የመሙላት ስራ ይከናወናል ብለዋል።

ምርትና ምርታማነትን በማጎልበት ተረጂነትን እንደሚያስቀሩ የተናገሩት ደግሞ በህዝባዊ ውይይቱ ተሳታፊ የሆኑት የሐረሪ ክልል ነዋሪዎች ናቸው።

በመድረኩ ላይ ከተሳተፉት መካከል ሼህ መሐመድ ሐሰን እንደገለጹት ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ (ዶ/ር) ያስጀመሩት የስንዴ ልማት ስራ "ከእርዳታ ተቀባይነት ወደ ረጂነት እንድንሸጋገር እንደሚያስችለን ተስፋ አለን ብለዋል።

ምርትና ምርታማነትን በማጎልበትና አብሮነትን በማጠናከር የተጀመሩ ስራዎችን አጠናክረው እንደሚቀጥሉም ሼህ መሐመድ ተናግረዋል።

መንግስት የያዛቸው የልማት ስራዎችን የሚያነቃቁና ህብረተሰቡንም እየጠቀሙ መሆናቸውን እና በበኩላቸውም ድጋፍ እያደረጉ መሆናቸውን የገለጹት ደግሞ አቶ አብዱረዛቅ ኡመር ናቸው።

አቶ አብዱረዛቅ አክለውም ከከርሰ ምድር ውሃ ተጠቅመው በሚያመርቱት የመስኖ ልማት ስራ ላይ የኤሌትሪክ ሃይል መቆራረጥ ተግዳሮት እየሆነባቸው እንደሚገኝና መፍትሄ እንዲሰጣቸው ጠይቀዋል።

በውይይቱም የተረጂነት አስተሳሰብ በግልም ሆነ በአገር ላይ የሚያደርሰው ጉዳትና መፍትሄዎቹ ላይ በመስራት ሁሉም ሚናውን ለመወጣት ስምምነት ላይ ተደርሷል።

በውይይቱ የሴቶችና ማህበራዊ ጉዳይ ሚኒስትር ዶክተር ኤርጎጌ ተስፋዬን ጨምሮ የጋምቤላ ክልል ምክትል ርዕሰ መስተዳድር አቶ ታንኳይ ጆክ፣ የሐረሪ ክልል ምክትል ርዕሰ መስተዳድር ወይዘሮ ሮዛ ኡመርና በየደረጃው ያሉ የክልሉ የስራ ሃላፊዎች እና የተለያዩ የማህበረሰብ ክፍሎች ተሳትፈዋል።

 

 

 

 

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም