ቀጥታ፡

የአክሱም አፄ ዮሐንስ አራተኛ አውሮፕላን ማረፊያ አገልግሎት መስጠት ጀመረ

አክሱም፤ ሰኔ 2/2016 (ኢዜአ)፦ የአክሱም አፄ ዮሐንስ አራተኛ አውሮፕላን ማረፊያ  ዛሬ በይፋ ተመርቆ ዳግም አገልግሎት መስጠት ጀመረ።

ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ (ዶ/ር) መጋቢት 6 ቀን 2016 ዓ.ም  ከትግራይ ክልል ከመጡ የኅብረተሰብ ተወካዮች ጋር ባደረጉት ውይይት መንግሥት በክልሉ ልማት እንዲረጋገጥ በትኩረት እየሰራ መሆኑን መናገራቸው ይታወሳል።

ከፕሪቶሪያው የሰላም ስምምነት በኋላ 45 ቢሊየን ብር በካሽ እንዲሁም 19 ቢሊየን ብር በዓይነት ለትግራይ ክልል ድጋፍ መደረጉንም ገልፀዋል። 

የትምህርት፣ የጤና፣ የመብራት፣ የቴሌኮምና ሌሎችም በርካታ መሠረተ-ልማቶች በፍጥነት ተገንብተው ለአገልግሎት እንዲበቁ መደረጉንም ተናግረዋል። 

በቀጣይም መንግሥት ከሚያከናውናቸው የልማት ሥራዎች ባሻገር በተለያዩ ባለድርሻ አካላት ትብብር የክልሉን ልማት ማፋጠን እንደሚገባ ገልፀዋል። 

የአክሱም አፄ ዮሐንስ አራተኛ አውሮፕላን ማረፊያን ዛሬ በይፋ የመረቁት የትግራይ ክልል ጊዜያዊ አስተዳደር ርዕሰ መስተዳደር አቶ ጌታቸው ረዳ ከኢትዮጵያ አየር መንገድ ግሩፕ ዋና ስራ አስፈፃሚ አቶ መስፍን ጣሰው ጋር በመሆን ነው።


 

የኢትዮጵያ  አየር መንገድ ግሩፕ ዋና ስራ አስፈፃሚ  መስፍን ጣሰው ፤ለአውሮፕላን ማረፊያው  እድሳት 290 ሚሊዮን ብር ወጪ ተደርጎለታል ብለዋል።

የአክሱም አፄ ዮሐንስ አራተኛ አውሮፕላን ማረፊያ  250 ሜትር የሚረዝም ማኮብኮብያ ያለውና ተርሚናሉ በአንድ ጊዜም 266 ተሳፋሪዎችን ማስተናገድ እንደሚችል ገልጸዋል።

የትግራይ ክልል ጊዜያዊ አስተዳደር ርዕሰ መስተዳድር አቶ ጌታቸው ረዳ በበኩላቸው፤ የአክሱም አፄ ዮሐንስ አራተኛ አውሮፕላን ማረፊያ አገልግሎቱን በይፋ መጀመሩ የሰላሙ ውጤት መሆኑን ገልጸው፤ አክሱም ሁሉን አቀፍ የቱሪስት መስህብ ያለው ከተማ ነው ብለዋል።

በቀጣይም በአክሱም የልማት ስራዎች እንደሚከናወን ተናግረዋል።

 

 

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም