ቀጥታ፡

በኢትዮጵያ የተፈጥሮ ፀጋዎችን በማልማት ዘላቂ ልማትን ማረጋገጥ ይገባል

ደብረ ብርሃን፤ ሰኔ 2/2016(ኢዜአ)፦ኢትዮጵያ ውስጥ በየአካባቢያው ያለውን እምቅ የተፈጥሮ ሀብት በማልማት ድህነትን በራስ አቅም በመፍታት ዘላቂ ልማትን ማረጋገጥ ይገባል ሲሉ በብልጽግና ፓርቲ የኦሮሚያ ክልል ቅርንጫፍ ጽህፈት ቤት የፖለቲካ ዘርፍ ሃላፊ ዶክተር ቢቂላ ሁሪሳ ተናገሩ።

"ከተረጅነት ወደ ምርታማነት ለተሟላ ሀገራዊ ሉዓላዊነትና ክብር" በሚል መሪ ሐሳብ በደብረ ብርሃን ከተማ የህዝብ ውይይት መካሄድ ጀምሯል።


 

በሰሜን ሸዋ ዞን ከሚገኙ ወረዳዎችና ከደብረ ብርሃን ከተማ ከተውጣጡ ነዋሪዎች ጋር ከፍተኛ የአመራር አባላቱ እየካሄዱ ያለው ውይይት ከተረጅነት ለመላቀቅና በቤተሰብ ደረጃ የምግብ ዋስትናን ለማረጋገጥ የሚያስችል አስተሳሰብ የሚፈጥር መድረክ ነው።

በብልጽግና ፓርቲ የኦሮሚያ ክልል ቅርንጫፍ ጽህፈት ቤት የፖለቲካ ዘርፍ ሃላፊ ቢቂላ ሁሪሳ (ዶ/ር) በዚሁ ወቅት እንደገለጹት፤ በኢትዮጵያ ስር ሰዶ የቆየውን ድህነት በራስ አቅም በመፍታት ዘላቂ ልማትን ማረጋገጥ ይገባል።

ተረጅነትና ልመና የአገሪቷን ክብር የሚቀንስ መሆኑን አውስተው፤ በአስተሳሰብ መዛነፍ ምክንያት ስር ሰዶ ከቆየው ድህነት ለመውጣት ዜጎች ሊረባረቡ እንደሚገባ ገልፀዋል ።

ኢትዮጵያ ያላትን አቅም በመጠቀም የእንስሳት ልማት፣ የአትክልትና ፍራፍሬ እንዲሁም የጓሮ አትክልት በስፋት በማምረት ከተረጅነት አስተሳሰብ በመላቀቅ የአገራችንን ክብር ማስጠበቅ ይገባል ብለዋል።

ስለሆነም በኢትዮጵያ ያለውን እምቅ የተፈጥሮ ሃብት በአግባቡ በማልማት ከድህነትና ኋላ ቀርነት በመላቀቅ ነፃነትን ማረጋገጥ ለነገ የማይባል ተግባር መሆኑን ጠቅሰው፤ ለዚህም በጋራ መረባረብ እንደሚገባ ተናግረዋል።


 

የደብረ ብርሀን ከተማ አስተዳደር ተቀዳሚ ምክትል ከንቲባ አቶ በድሉ ውብሸት በበኩላቸው፤ በየአካባቢው ያልተነካና ሰርቶ ለመለወጥ የሚያስችሉ ሰፊ ሀብትና የስራ እድል መኖሩን ተናግረዋል።

ባለፉት ወራቶች በከተማዋና አካባቢው በፀጥታ ችግር ውስጥ ሆኖም በሌማት ትሩፋት የተጀመሩ ስራዎች ውጤት የታየባቸው መሆኑን ጠቅሰው፤ ይህም ተጠናክሮ እንደሚቀጥል ገልፀዋል።

ህዝቡም ተረጂነት አስነዋሪ መሆኑን በመረዳት ብልፅግናን ለማረጋገጥ በሚደረገው ጥረት ሁሉ መትጋት እንደሚገባ አስገንዝበዋል።

በመድረኩ በየደረጃው ያሉ የአመራር አባላት፣ የደብረ ብርሃን ከተማና የሰሜን ሽዋ ዞን ነዋሪዎች በመሳተፍ ላይ ይገኛሉ።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም