በትግራይ ክልል መቀሌ ከተማ ባዛርና አውደ ርዕይ እየተካሄደ ነው - ኢዜአ አማርኛ
በትግራይ ክልል መቀሌ ከተማ ባዛርና አውደ ርዕይ እየተካሄደ ነው

መቀሌ ፤ ሰኔ 2/2016(ኢዜአ)፦ በኢትዮጵያ ታምርት ንቅናቄ የተገኘውን የኢንዱስትሪ ልማት በዘላቂነት ለማጠናከርና በትግራይ ክልል ልማትን የማነቃቃት ዓላማ ያለው ባዛርና አውደ ርዕይ በመቀሌ ከተማ እየተካሄደ ነው።
"የኢትዮጵያ ታምርት፣እኛም እንሸምት" እና ሁለተኛው ዙር አገር አቀፍ የትግራይ ክልል ኢንዱስትሪ ንቅናቄ ሳምንት አካል የሆነ ባዛርና አውደ ርዕይ በመቀሌ ከተማ እየተካሄደ ነው ።
የኢንዱሰትሪ ሚኒስትር ዴኤታ አቶ ሀሰን መሐመድ በዚሁ ወቅት እንደገለጹት፤ ባዛሩና አውደ ርዕዩ በኢትዮጵያ ታምርት ንቅናቄ የተገኘውን የኢንዱስትሪ ልማት በዘላቂነት ለማጠናከርና የትግራይ ክልል ልማትን ለማነቃቃት ያለመ ነው።
መንግስት አገር በቀል አምራች ኢንዱስትሪዎችን በማስፋፋት የአገር ውስጥ ምርትን ለማሳደግና ለመጠቀም በትኩረት እየሰራ መሆኑንም ተናግረዋል ።
በተለያዩ ምክንያቶች ኢንዱስትሪዎች ወደ ልማት እንዲመለሱና አዳዲሶችም እንዲከፈቱ አስፈላጊው ድጋፍ እየተደረገ መሆኑን ሚኒስትር ዴኤታ አቶ ሀሰን ገልፀዋል።
መንግስት የአስር ዓመት የኢኮኖሚ መዋቅራዊ ሽግግር እቅድን ለማሳካት በአምራች ኢንዱስትሪው የሚያጋጥሙ እንደ ብድር፣ ፋይናንስና ማሽነሪ አቅርቦት እንዲሁም የመሬትና የስራ ክህሎት ችግሮችን ለመፍታት ኮሚቴ አቋቁሞ ከባለድርሻ አካላት ጋር በትብብር እየሰራ መሆኑንም አስረድተዋል።
የትግራይ ክልል ጊዚያዊ አስተዳደር ርዕሰ መስተዳድር አቶ ጌታቸው ረዳ በበኩላቸው ፤ ሁለተኛው ዙር አገር አቀፍ የትግራይ ክልል የኢንዱስትሪ ንቅናቄ ሳምንት በክልሉ የተጀመሩ የልማት ስራዎችን ለማጠናከርና ለማነቃቃት ትልቅ ሚና አለው ብለዋል ።
በክልሉ በአምራች ኢንዱስትሪው ዘርፍ እያጋጠሙ ያሉትን ችግሮች ለመፍታት ከፌዴራል መንግስት ጋር በትብብር እየተሰራ መሆኑንም ጠቁመዋል።
በሁለተኛው ዙር አገር አቀፍ የትግራይ ክልል ኢንዱስትሪ ንቅናቄ ሳምንት በክልሉ ኢንዱስትሪ ዘርፉን የሚያነቃቁ መርሃ ግብሮች መዘጋጀታቸውን የተናገሩት የትግራይ ክልል ጊዚያዊ አስተዳደር ኢንዱስትሪ ቢሮ ሀላፊ ገብረህይወት ዓገባ(ዶ/ር) ናቸው።
በመቀሌ ከተማ እየተካሄደ ያለው ባዛርና አውደ ርዕይ በኢንዱስትሪ ሚኒሰቴርና በትግራይ ክልል ጊዜያዊ አስተዳደር ኢንዱስትሪ ቢሮ ትብብር የተዘጋጀ ነው።
በዝግጅቱ ከ150 በላይ አምራቾች እየተሳተፉ ሲሆን፤ ለአምስት ቀን እንደሚቆይ ታውቋል።