ቀጥታ፡

የተግባርና ንድፈ-ሃሳብ ስልጠና ሲከታተሉ የቆዩ የደንብ ማስከበር አመራርና ኦፊሰር አባላት ተመረቁ

አዲስ አበባ፤ ሰኔ 2/2016(ኢዜአ)፦ የአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር በኢትዮጵያ ፖሊስ ዩኒቨርሲቲ ወታደራዊ የተግባርና ንድፈ-ሃሳብ ስልጠና ሲከታተሉ የቆዩ የደንብ ማስከበር አመራርና ኦፊሰር አባላትን አስመረቀ። 

በምርቃት ሥነ-ስርዓቱ ላይ የአዲስ አበባ ሰላምና ፀጥታ አስተዳደር ቢሮ ኃላፊ ሊዲያ ግርማ፣ የኢትዮጵያ ፖሊስ ዩኒቨርሲቲ ፕሬዚዳንት ምክትል ኮሚሽነር ጄኔራል መስፍን አበበ የአዲስ አበባ ደንብ ማስከበር ባለስልጣን ሥራ አስኪያጅ ሻለቃ ዘሪሁን ተፈራ ተገኝተዋል፡፡


 

እንዲሁም በአዲስ አበባ ከተማ ምክር ቤት የሰላም፣ ፍትሕና መልካም አስተዳደር ጉዳዮች ቋሚ ኮሚቴ ሰብሳቢ አቶ ሙሉነህ ደሳለኝ፣ የፌደራል ፖሊስ መኮንኖች፣ የሰንዳፋ በኪ ከተማ የስራ ኃላፊዎች፣ ነዋሪዎች እና ጥሪ የተደረገላቸው አካላት ተገኝተዋል። 

ለምርቃት የበቁት የደንብ ማስከበር አመራርና ኦፊሰር አባላት የመዲናዋን የደንብ መተላለፍና ህገ-ወጥነት መቆጣጠር የሚያስችል ከአንድ ወር በላይ የቆየ ወታደራዊ የተግባርና ንድፈ-ሃሳብ ስልጠና ሲከታተሉ መቆየታቸው ተገልጿል። 

የምርቃት ሥነ-ስርዓቱም በኢትዮጵያ ፖሊስ ዩኒቨርሲቲ ቅጥር ግቢ " በደንብ ማስከበር ፓራ ሚሊተሪ ኦፊሰሮቻችን እና በህብረተሰብ ሁሉን አቀፍ ተሳትፎ የደንብ መተላለፍና ህገወጥ ተግባራትን በመቆጣጠር የአዲስ አበባ ከተማን ለነዋሪዎቿ ምቹ፣ ማራኪና ሰላማዊ እንድትሆን እናደርጋታለን" በሚልና በሌሎች መሪ መልዕክቶች ተካሂዷል።

 

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም