ቀጥታ፡

በክረምቱ ወቅት የዓሣ ማስገሩን ሥራ ዝግ አድርጎ ማልማት ዓሣን በብዛት ለማምረት ይረዳል - የዘርፉ ባለሙያዎች

ጋምቤላ/አርባምንጭ/ባህርዳር ፤ ሰኔ 2 /2016(ኢዜአ)፦ በክረምቱ ወቅት የዓሣ ማስገሩን ሥራ ዝግ አድርጎ አካባቢውን በአረንጓዴ ማልማት ዓሣን በቀጣይነት በብዛት ለማምረት እንደሚረዳ በዘርፉ የተሰማሩ ባለሙያዎችና የሥራ ሃላፊዎች ገለጹ።

በሌማት ትሩፋት መርሃ ግብር የቤተሰብ ሥርዓተ ምግብን የተሟላ ለማድረግ ትኩረት ከተሰጣቸው መካከል የእንስሳትና ዓሣ ሀብት ልማት አንዱ ነው።

ኢትዮጵያ ደግሞ የአፍሪካ ቀንድ የውሃ ማማ፣ የታላቁ ስምጥ ሸለቆ ሃይቆች በብዛት ያሉባት፣ የበርካታ ሃይቆች፣ ወንዞችና ኩሬዎች ባለቤት ናት።

በተፈጥሮ ካሉ የውሃ አካላት በተጨማሪ ሰው ሰራሽ ኩሬዎችና ገንዳዎችን በማበጀትም ዓሣን በዘመናዊ መልኩ ማምረት ይቻላል።

አገሪቷ ባሏት የዓሣ ሀብት አቅም ልክ አምርታ በመጠቀሙ ረገድ ገና ብዙ መሰራት የሚገባት ሥራዎች እንዳሉ እሙን ነው።

የዓሣ ሀብት ልማት ላይ የወቅቶች መፈራረቅ በምርቱ ላይ ልዩነት እንደሚያሳይ በዘርፉ የተሰማሩት ባለሙያዎች ይገልጻሉ። 

በአገሪቷ በከፍተኛ የዓሣ ምርታቸው ከሚታወቁት አካባቢዎች ባህርዳር፣ ጋምቤላና አርባ ምንጭ አካባቢ ከመስኩ ጋር ቅርበት ያላቸው ባለሙያዎች ከኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት ጋር ቆይታ አድርገዋል።

እንደ ባለሙያዎቹ ገለፃ በተለይም ከመጋቢት ወር አንስቶ እስከ ሐምሌ ወር መጨረሻ አካባቢ ለዓሣዎች የርቢ ወቅት በመሆኑ በክረምቱ ወቅት ዓሣን በቀላሉ ማምረት አይቻልም።


 

የጋምቤላ ክልል የእንስሳትና ዓሣ ሀብት ልማት ቢሮ ሃላፊ አቶ ኦካች ባሉቴ ወንዞችም ሆኑ ኩሬዎች በክረምቱ በጎርፍ ስለሚሞሉ ዓሣዎችን እንደ በጋው ወራት በአንድ አካባቢ ተከማችተው በግላጭ አናገኛቸውም ብለዋል።

በደቡብ ኢትዮጵያ ክልል ጋሞ ዞን ግብርና መምሪያ የዓሣ ሀብት ልማት ባለሙያ አቶ ይድነቃቸው ሉዋ  በክረምት ወቅት ሃይቆቹ በደለል ምክንያት ስለሚደፈርሱና የምግብ ሰንሰለታቸው ላይ መዛባትና መረበሽ ስለሚፈጠር ከበጋው ወራት አንፃር የምርት መቀነስ ይከሰታል ብለዋል።

እንደ አቶ ይድነቃቸው ገለጻ በክረምቱ ወራት ለዓሣዎቹ ምርት መቀነስ ዋናው ምክንያት ወቅቱ ለዓሣዎቹ የርቢ ወቅት ስለሆነ ዕንቁላል ወደ ሚጥሉባቸው አካባቢዎች ርቀው ስለሚሸሸጉ ነው ይላሉ፡፡

የአርባ ምንጭ ዓሣ አስጋሪዎች ስፔሻላይዝድ መሠረታዊ ህብረት ሥራ ማህበር ሊቀመንበር አቶ ዳዊት ደጾም የክረምቱ አየር ፀባይ መለዋወጥ ለዓሣ ምርት መቀነስ ምክንያት መሆኑን ያጠናክራሉ።

ይኸን የመራቢያ ወቅት ጠብቀው በተለይም የጣና ሃይቅ ዓሣ አስጋሪዎች ከማስገር እንዲታቀቡ እንደሚደረግ ያነሱት ደግሞ በአማራ ክልል የእንስሳትና ዓሣ ሃብት ልማት ጽህፈት ቤት የዓሣ ባለሙያ አቶ አበበ ፈንታሁን ናቸው።


 

በክረምቱ ወቅት የዓሣ ማስገሩን ሥራ ዝግ አድርጎ ማለፉ  በቀጣዩ ወራት ምርቱን  በብዛት ለማግኘት እንደሚያግዝ የሚገልጹት ደግሞ በጋምቤላ ክልል እንስሳትና ዓሣ ሀብት ልማት ቢሮ የእንስሳትና ዓሣ እርባታ ዳይሬክተር አንተነህ ተስፋዬ ናችው።

በአሁኑ ጊዜ ዘመናዊ የሆነ የዓሣ ሀብት አስተዳደር  'ኮ ማናጅሜንት"  ወይም አሳታፊ የዓሣ ሀብት አስተዳደር በሚባለው ሥርዓት ማስገሪያ መሣሪያዎችን ጨምሮ የሚሰገርባቸው ወቅቶች ይለያሉ ብለዋል።

በዚህም ዓሣው ሳይጎዳ በዘለቄታው ምርቱ እንዳይቀንስና ጨርሶም ሳይጠፋ ቀጣይነት እንዲኖረው ለማስቻል የሚከናወን ተግባር መሆኑን ተናግረዋል።

ከዚህ ሌላ ዓሣዎች ያሉባቸውን ኩሬዎችንም ሆነ የወንዞቹን አካባቢ አረንጓዴ አልብሶ ማልማት ወቅቱን ተከትሎ የውሃማ ስፍራዎቹ ዳርቻ ገላጣ ሆኖ ዓሣዎቹን ለአውሬ እንዳይጋለጡ እንደሚረዳ አቶ አንተነህ ተናግረዋል።

 

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም