ኢትዮጵያ ከጅቡቲ ጋር ዛሬ ትጫወታለች

አዲስ አበባ፤ ሰኔ 2/2016(ኢዜአ)፦ በ23ኛው የፊፋ ዓለም ዋንጫ ማጣሪያ ኢትዮጵያ አራተኛ የምድብ ጨዋታዋን ከጅቡቲ አቻዋ ጋር ዛሬ ታደርጋለች።

የሁለቱ አገራት ጨዋታ ከምሽቱ 1 ሰዓት ላይ በሞሮኮ ኤል ጃዲዳ ከተማ በሚገኘውና 15 ሺህ ተመልካች በሚያስተናግደው ኤል አብዲ ስታዲየም ይከናወናል።

ቡድኑ ከጅቡቲ ጋር ለሚያያደርገው ጨዋታ ትናንት ሞሮኮ የገባ ሲሆን ልምምዱንም ጨዋታው በሚደረግበት ስታዲየም ማከናወኑን ኢዜአ ከኢትዮጵያ እግር ኳስ ፌዴሬሽን ያገኘው መረጃ ያመለክታል።

በአሰልጣኝ ገብረመድህን ኃይሌ የሚመራው የኢትዮጵያ ብሔራዊ ቡድን በዓለም ዋንጫ የአፍሪካ ዞን ማጣሪያ በምድብ አንድ ከግብጽ፣ ጊኒ ቢሳው፣ ቡርኪናፋሶ፣ ሴራሊዮንና ጅቡቲ ጋር ተደልድሎ ጨዋታውን እያደረገ ይገኛል።

ዋልያዎቹ ሐሙስ ግንቦት 29 ቀን 2016 ዓ.ም ከጊኒ ቢሳው ጋር ባደረጉት የምድቡ ሶስተኛ ጨዋታ ያለ ምንም ግብ አቻ ተለያይተዋል።

ኢትዮጵያ እስከ አሁን ባደረገቻቸው ሶስት ጨዋታዎች 2 ነጥብ በመያዝ 5ኛ ደረጃ ላይ ትገኛለች።

ተጋጣሚዋ ጅቡቲ በምድቡ 3 ጨዋታዎችን አድርጋ በ3ቱም ሽንፈት አጋጥሟታል። ያለ ምንም ነጥብ በምድቡ የመጨረሻውን 6ኛ ደረጃ ይዛለች።

በፊፋ ወርሃዊ የአገራት የእግር ኳስ ደረጃ ኢትዮጵያ 145ኛ፤ ጅቡቲ 192ኛ ደረጃ ላይ ተቀምጠዋል።

ዩጋንዳዊው አሊ ሳሊባ የሁለቱን አገራት ጨዋታ በዋና ዳኝነት ይመሩታል።

በምድብ አንድ ጊኒ ቢሳው ከግብጽ እና ቡርኪናፋሶ ከሴራሊዮን ነገ በተመሳሳይ ከምሽቱ 1 ሰዓት ላይ ጨዋታቸውን ያደርጋሉ።

ግብጽ ምድቡን በ9 ነጥብ ስትመራ ጊኒ ቢሳው በ5 ነጥብ 2ኛ ደረጃን ይዛ ትከተላለች። ቡርኪናፋሶና ሴራሊዮን በተመሳሳይ 4 ነጥብ በግብ ክፍያ ተበላልጠው 3ኛ እና 4ኛ ደረጃ ላይ ተቀምጠዋል።

45 የአፍሪካ ሀገራት በዘጠኝ ምድብ ተከፍለው የዓለም ዋንጫ ማጣሪያ ጨዋታቸውን በማድረግ ላይ ይገኛሉ።

አፍሪካ በዓለም ዋንጫ ታሪክ ለመጀመሪያ ጊዜ 9 አገራት የምታሳትፍ ሲሆን በተጨማሪም በሌላ አህጉር ከሚገኝ አገር ጋር የጥሎ ማለፍ ጨዋታ አድርጎ ያሸነፈ አገር አህጉሪቷን ወክሎ የሚሳተፍ 10ኛ ቡድን ይሆናል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም