የሰውነት ቅርፅ መገንባት ስፖርትን ለማሳደግ የኅብረተሰቡን ግንዛቤን መጨመርና ስፖርቱን በገንዘብ መደገፍ ያስፈልጋል

አዲስ አበባ፤ ሰኔ 2/2016(ኢዜአ)፦  የሰውነት ቅርፅ መገንባት ስፖርትን ለማሳደግ የኅብረተሰቡን ግንዛቤን መጨመርና ስፖርቱን በገንዘብ መደገፍ እንደሚያስፈልግ የዘርፉ ባለሙያዎች ገለፁ ። 

ዓለም አቀፉ የአካል ብቃትና የሰውነት መገንባት ፌዴሬሽን እንደ አውሮፓውያን አቆጣጠር በ1946 ዓ.ም በካናዳ ሞንትሪያል የተመሰረተ ሲሆን፤ ዋናው ቢሮ በስፔን ማድሪድ ይገኛል።

የኢትዮጵያ ክብደት ማንሳት እና ሰውነት መገንባት ፌዴሬሽን ፤ እንደ አውሮፓውያን አቆጣጠር በ1962 ዓ.ም በወቅቱ አጠራር በወወክማ፤ የስፖርት ማዘውተሪያ መቋቋሙ ይታወቃል፡፡

ፌዴሬሽኑ እንደ አውሮፓውያን አቆጣጠር በ2023፤ የዓለም አቀፉ የአካል ብቃትና የሰውነት ግንባታ ፌዴሬሽን አባል ሆኖ መመዝገቡ፤ ለስፖርት ዘርፉ ማደግ ከፍተኛ አስተዋፅኦ እያበረከተ ነው።

ስፖርቱ በሚፈለገው መንገድ እንዲያድግ የግንዛቤ ማስጨበጥ ሥራው ማደግ እንዳለበት ባለሙያዎች ይናገራሉ ።

የዘርፉ የስፖርት ባለሙያዎችና፤ ዓለምአቀፍ የሰውነት ቅርፅ ተወዳዳሪ የሆኑት ኤደን ሸፈራውና ዮናስ ግርማ ለኢዜአ እንደገለፁት ስፖርቱ የራሱ መመሪያና አካሄድ አለው ።

የሰውነት ቅርፅ ስፖርት ጂም ውስጥ ብቻ ገብቶ መሥራት ማለት እንዳልሆነና በሥነ-ምግብ፣ በትክክለኛ ባለሙያ መሰልጠንና መሥራትን እንደሚጠይቅ ይናገራሉ።

ስፖርቱን ለማሳደግ ደግሞ የማኅበረሰቡን አመለካከት መቀየርና  ስፖርቱን በገንዘብ መደገፍ እንደሚያስፈልግ ገልፀዋል።   

ኢትዮጵያ ዓለም አቀፉ የአካል ብቃትና የሰውነት መገንባት ፌዴሬሽን አባል ስለሆነችና፤ የተለያዩ ውድድሮች የመሳተፍ እድሉ ስላላትም የውድድር አማራጮች እንዳሉ ገልፀዋል።

ነገር ግን ከገንዘብ ጋር በተያያዘ ችግር ተወዳዳሪዎች የውድድር ተሳትፎ ማጣት እንደሌለባቸው አንስተዋል።

አራተኛው ሀገር አቀፍ የሰውነት ቅርፅ ስፖርት ውድድር በኢትዮጵያ ስፖርት አካዳሚ ከግንቦት 20 እስከ 22 ቀን 2016 ዓ.ም መከናወኑ የሚታወስ ነው።

 

 

 

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም