የኢትዮጵያ አየር መንገድ ነገ ሰኔ 2 ወደ አክሱም በረራ ይጀምራል - ኢዜአ አማርኛ
የኢትዮጵያ አየር መንገድ ነገ ሰኔ 2 ወደ አክሱም በረራ ይጀምራል
አዲስ አበባ፤ ሰኔ 1/2016 (ኢዜአ)፦ የኢትዮጵያ አየር መንገድ ነገ ሰኔ 2/2016 ወደ ትግራይ ክልል አክሱም ከተማ በረራ እንደሚጀምር ገለጸ።
የአየር መንገዱ የንግድ ዘርፍ ዋና ኃላፊ ለማ ያዴቻ ከጥቂት ጊዜ በፊት አየር መንገዱ ዳግም ወደ አክሱም በረራ እንደሚጀምር ለኢዜአ መግለጻቸው ይታወሳል።
ዳግም በረራውን ለማስጀመር የሚያስችሉ ቅድመ ዝግጅቶች ሲደረግ መቆየቱንም እንዲሁ።
በመሆኑም አየር መንገዱ ከነገ ሰኔ 2/2016 ዓ.ም ጀምሮ ታሪካዊ የቱሪዝም መዳረሻ ወደ ሆነችው የአክሱም ከተማ በረራ እንደሚያደርግ አስታውቋል።
በረራም በየቀኑ 1 ጊዜ የሚደረግ ሲሆን በቀጣይ የደንበኞች ፍላጎት መሰረት በማድረግ በቀን ወደ 3 ጊዜ ለማሳደግ እንደሚሰራ ተገልጿል።
የበረራው መጀመር በአክሱም ከተማ ቀደም ሲል የነበረውን የቱሪስት ፍሰት ለመጨመርና ማኅበራዊ መስተጋብርን ለማጠናከር ያስችላል ተብሏል።