ቀጥታ፡

ወጣቶች በበጎ ፈቃድ አገልግሎት ደም በመለገስና ሌሎች እንዲለግሱ በማነሳሳት ግንባር ቀደም እንዲሆኑ ተጠየቀ

አዳማ፤፤ ሰኔ 1/2016(ኢዜአ)፡- ወጣቶች በበጎ ፈቃድ አገልግሎት ደም በመለገስና ሌሎችም እንዲለግሱ  በማነሳሳት ግንባር ቀደም ተዋንያን እንዲሆኑ የኢትዮጵያ ደምና ህብረ ህዋስ ባንክ አገልግሎት ጠየቀ፡፡

አገልግሎቱ  ከኢትዮጵያ ወጣቶች ብሔራዊ ደም ለጋሾች ማህበር ጋር በመተባበር የክረምት የደም ማሰባሰብ በጎ ፈቃድ አገልግሎት ማስጀመሪያ መርሃ ግብር ዛሬ በአዳማ ከተማ አከናውኗል፡፡

ባንኩ በአራት ወራት ውስጥ 120ሺህ ዩኒት ደም የሚያሰባስብበት መርሃ ግብር ዛሬ ይፋ አድርጓል።


 

የኢትዮጵያ ደምና ህብረ ህዋስ ባንክ  አገልግሎት ዋና ዳይሬክተር ዶክተር አሸናፊ ታዘበው በዚሁ ወቅት እንደገለጹት ፤ ደም ልገሳን በክረምት ከሚተገበሩ የበጎ ፈቃድ አገልግሎት መርሃ ግብር አካል እንዲሆኑ አድርጓል።

መርሃ ግብሩ በተለያዩ ችግሮች የሚያጋጥመውን የደም እጥረት ለማቃለልና በደም እጦት ሳቢያ ሕይወት እንዳያልፍ ታልሞ መዘጋጀቱን ተናግረዋል፡፡

አገልግሎቱ  በአሁኑ ወቅት በትራፊክ አደጋ፣ በእናቶች ወሊድ፣ በተለያዩ ሕመሞች በሚፈጠር የደም እጥረት እንዳያጋጥም ከተለያዩ ተቋማትና የህብረተሰብ ክፍሎች ጋር በመስራት ላይ እንደሚገኝ አመልክተዋል።

ወጣቶች የደም ልገሳን ባህላቸው በማድረግ እንዲቀጥሉ በዘርፉ እየገጠመ ያለውን እጥረት በማቃለል  ሀገራዊ ግዴታቸውን እንዲወጡም ዋና ዳይሬክተሩ ጠይቀዋል፡፡ 

አገልግሎቱ ከዛሬ ጀምሮ እስከ መስከረም 30/2017 ዓ.ም ድረስ 120 ሺህ ከረጢት ደም ለማሰባሰብ አቅዶ ወደ ስራ መግባቱንም አስታውቀዋል፡፡

ወጣቶቹ  በራሳቸው ከሚለግሱት ደም በተጨማሪም ኅብረተሰቡ ደም እንዲለግስ በማነቃቃትና በማስተማር ህይወት የማዳን በጎ ተግባር እንዲተባበር ጥሪ አቅርበዋል፡፡

የኢትዮጵያ  ወጣቶች ብሔራዊ ደም ለጋሾች ማህበር ሰብሳቢ ወጣት ነብዩ ሙሰማ ፤ የማህበሩ  አባላት በቋሚነት ከሚለግሱት በተጨማሪ ሕዝቡ ደም እንዲለግስ በማነቃቃት ቅስቀሳ እንደሚያደርጉ ገልጿል፡፡


 

''ደም የሚያስፈልገውን ሰው ህይወት ማዳን የሚቻለው በሚያስፈልገው ጊዜ ደም እንዲያገኝ በመርዳት ብቻ ነው'' የሚለው ወጣት ነብዩ፣ከማህበሩ አባላት ጋር መርሃ ግብሩን ለማሳካት ጥረት ይደረጋል ብሏል። 

የማህበሩ አባል ወጣት መቅደስ ግዛው ፤ በደም እጦት ችግር የሰው ህይወት እንዳያልፍ የድርሻዋን ለመወጣት መነሳቷን ገልጻለች።


 

በተለይም እናቶች በወሊድ ወቅት የደም እጥረት እንዳይገጥማቸው ትኩረት ሰጥታ እንደምትንቀሳቀስ ተናግራለች።

 

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም