በአዲስ አበባ ወደ ቴክኒክና ሙያ ትምህርት የሚገቡ ዜጎችን ለማማከር የሚያስችል ሰነድ ይፋ ሆነ - ኢዜአ አማርኛ
በአዲስ አበባ ወደ ቴክኒክና ሙያ ትምህርት የሚገቡ ዜጎችን ለማማከር የሚያስችል ሰነድ ይፋ ሆነ
አዲስ አበባ፤ ሰኔ 1/2016(ኢዜአ)፡- የሥራና ክህሎት ሚኒስቴር ወደ ቴክኒክና ሙያ ትምህርት የሚገቡ ዜጎች በየደረጃው ውጤታማ ለመሆን የማማከር አገልግሎት ለመስጠት የሚያስችል ሰነድ በአዲስ አበባ ደረጃ ይፋ አደረገ።
በሚኒስቴሩ የሥልጠና ባለሙያ ይታያቸው ደሊል በዚሁ ጊዜ እንደገለጹት፤ ወደ ቴክኒክና ሙያ የሚገቡ ዜጎች ዝንባሌያቸው ተለይቶ ሥልጠና እንዲወስዱ ማድረግ ይገባል ብለዋል።
ለዚህም የማማከር አገልግሎት መስጠት ተገቢ መሆኑን በመገንዘብ በአገር አቀፍ ደረጃ ለተግባራዊነቱ እየተሰራ መሆኑን ገልፀዋል።
የማማከር አገልግሎት ኢንዱስትሪው የሚፈልገውን የሰው ኃይል ለማፍራትና ሰልጣኞቹም አስፈላጊ ክህሎት ይዘው በፍጥነት ወደ ሥራ እንዲገቡ እንደሚያግዛቸው ጠቁመዋል።
ይህንንም ተከትሎ ሰነዱ ተዘጋጅቶ በአዲስ አበባ ደረጃ ዛሬ ይፋ መሆኑን ጠቁመው፤ የማማከር ሥራው በዘርፉ ልምድ ባካበቱ ሙያተኞች የሚካሄድ መሆኑንም ነው ያስረዱት።
ሰነዱ የዘርፉን ተፈላጊነት በመጨመርና የኃብት ብክነትን በመቀነስ ትልቅ አስተዋጽዖ እንደሚያደርግ ገልፀዋል።
ሰነዱን ያቀረቡት አቶ አባይነህ መኮንን በበኩላቸው፤ የተዘጋጀው ሰነድ የቴክኒክና ሙያ ተቋማት የተሻለና ውጤታማ ሥልጠና ለመስጠት የሚያስችላቸው ነው ብለዋል።
ሰነዱ ለሰልጣኞች ከሚሰጠው ሙያዊ እውቀት ጎን ለጎን ተቋማቱ የማማከር ሥራ እንዲሰሩ የሚያደርግ ሲሆን፤ ከኢንዱስትሪው ጋር የሚያስተሳስራቸው መሆኑንም አብራርተዋል።
የማማከር አገልግሎቱ ሰልጣኞች ትምህርት ከመጀመራቸው በፊት፣ ትምህርት ላይ እያሉና ትምህርታቸውን አጠናቀው ሲመረቁ ማግኘት እንዳለባቸው በሰነዱ ተመላክቷል ነው ያሉት።