ዜጎችን በማሳተፍ ሀገራዊ መግባባት ለመፍጠርና ዘላቂ ሰላም ለመገንባት በቅንጅት እየተሰራ ነው - ሰላም ሚኒስቴር - ኢዜአ አማርኛ
ዜጎችን በማሳተፍ ሀገራዊ መግባባት ለመፍጠርና ዘላቂ ሰላም ለመገንባት በቅንጅት እየተሰራ ነው - ሰላም ሚኒስቴር
አዲስ አበባ፤ ሰኔ 1/2016(ኢዜአ)፡- ዜጎችን በሀገራዊ ጉዳይ በማሳተፍ ሀገራዊ መግባባት ለመፍጠርና ዘላቂ ሰላም ለመገንባት በቅንጅት እየተሰራ መሆኑን የሰላም ሚኒስትር ዴኤታ ከይረዲን ተዘራ (ዶ/ር) ገለፁ።
ሀገር አቀፉ ''ሰላም ለሁሉም፤ ሁሉም ለሰላም'' የ5 ኪሎ ሜትር የጎዳና ላይ የሩጫ ውድድር ሰኔ 23 ቀን 2016 ዓ.ም ሊያካሂድ መሆኑን የሰላም ሚኒስቴር ገልጿል።
የሰላም የሩጫ ውድድሩ የሰላም ሚኒስቴር፣ የባህልና ስፖርት ሚኒስቴር፣ የኢትዮጵያ አትሌቲክስ ፌዴሬሽን፣ የታላቁ ሩጫ በኢትዮጵያ ጨምሮ የክልል የባህልና ስፖርት ቢሮዎች ጋር በመተባበር የሚካሄድ ነው ተብሏል።
የሩጫ ውድድሩ በሰላም ሚኒስቴር አዘጋጅነት በከተማ አስተዳደሮችና በክልል ከተሞች በተመሳሳይ ጊዜ የሚካሄድ ሲሆን፤ በዚህም ታዋቂ አትሌቶችን ጨምሮ በርካታ ሰዎች እንደሚሳተፉበት ተገልጿል።
ውድድሩን አስመልክቶ ዛሬ በተዘጋጀው መርኃ ግብር፤ የሰላም ሚኒስትር ዴኤታ ከይረዲን ተዘራ (ዶ/ር) እንደገለጹት፤ የሩጫ ውድድሩ ዜጎችን በማሳተፍ ብሔራዊ መግባባት ለመፍጠር፣ አብሮነትን በማጠናከርና ዘላቂ ሰላምን ለመገንባት ያለመ መሆኑን ተናግረዋል።
ይህም ብቻ ሳይሆን መንግሥት ለሰላም ያለውን ቁርጠኝነት ለማሳየት የተዘጋጀ እንደሆነም ገልፀዋል።
በሩጫ ውድድሩ ዜጎች የእርስበርስ ግንኙነትንና ሕብረ-ብሔራዊ አንድነታቸውን በማጠናከር ለሰላም ግንባታ የበኩላቸውን እንዲወጡ ለማድረግ ያለመ መሆኑንም ጠቁመዋል።
ስፖርት የአንድነት፣ የፍቅርና የአብሮነት እሴት የሚንፀባረቅበት መሆኑን በመግለፅ፤ ሰላምን ለመገንባት ለሚደረገው ጥረትም ወሳኝ ሚና እንዳለውም ነው የጠቆሙት።
ዜጎችን በአገራዊ ጉዳይ ንቁ ተሳትፎ በማድረግ የሚያጋጥሙ አለመግባባቶችን በውይይትና በንግግር የመፍታት ባህል እንዲያድግ በትኩረት እየተሰራ ነው ብለዋል።
ሀገራዊ መግባባትን ለመፍጠርና ዘላቂ ሰላም ለመገንባት ዜጎች በሀገራዊ ጥቅምና እሴት የተቀራረበ ግንዛቤ እንዲኖራቸው በቅንጅት እየተሰራ መሆኑን ገልፀዋል።
በመርኃ-ግብሩ የተሳተፉ የክልል ባህል፣ ስፖርትና ወጣቶች ቢሮ ተወካዮች ስፖርት ከአካል እንቅስቃሴ ባለፈ ለሰላምና ለልማት ትልቅ አስተዋፅዖ እንዳለው ተናግረዋል።
የሰላም የሩጫ ውድድርም ሀገራዊ ሰላምና አንድነትን ለማጠናከር ያለመ መሆኑን ገልጸው፤ የሩጫ ውድድሩ በስኬት እንዲጠናቀቅ የበኩላቸውን ሚና እንደሚወጡ አረጋግጠዋል።
በስፖርት ማህበረሰቡ ያለው የመተባበርና የመደጋገፍ አቅም ከፍተኛ መሆኑን በመግለፅ ዘላቂ ሰላምን ለመገንባትና አንድነትን ለማጠናከር ቀጣይነት ባለው መልኩ ትኩረት እንደሚሰሩ ገልፀዋል።
የክልል ሰላምና ፀጥታ ቢሮ ኃላፊዎች የሚካሄደው የሰላም የሩጫ ውድድር በሰላም ተከናውኖ ውድድሩ የታለመለትን ግብ እንዲመታ የተሰጣቸውን ኃላፊነት እንደሚወጡ ገልፀዋል።
በውድድሩ ለሚያሸንፉ ተወዳዳሪዎች ከ10 ሺህ እስከ 50 ሺህ ብር የገንዘብ ሽልማት መዘጋጀቱም ተገልጿል።