ቀጥታ፡

ታንዛኒያ በሰላምና ደኅንነት ዘርፍ ከኢትዮጵያ ጋር ያላትን ትብብር ታጠናክራለች  

አዲስ አበባ፤ ሰኔ 1/2016(ኢዜአ)፡-ታንዛኒያ በሰላምና ደኅንነት ዘርፍ ከኢትዮጵያ ጋር ያላትን ትብብር ለማጠናከር  እንደምትሰራ የአገሪቱ የመከላከያና ብሔራዊ አገልግሎት ሚኒስትር ስቴርጎሜና ላውረንስ ተናገሩ።

ሚኒስትሯ ከኢዜአ ጋር በነበራቸው ቆይታ፤ ታንዛኒያና ኢትዮጵያ በሰላምና ጸጥታ ዘርፍ ያላቸው ታሪካዊ ትብብር አሁንም ተጠናክሮ መቀጠሉን ገልፀዋል።

ሁለቱ አገራት በሰላምና ጸጥታ ዙሪያ በትብብር ለመሥራት የተፈራረሙትን የመግባቢያ ሥምምነት ተግባራዊ እያደረጉ መሆኑንም አስታውሰዋል። 

ታንዛኒያ በቀጣናው እንዲሁም በአህጉር ደረጃ ሰላምና ጸጥታን ለማረጋገጥ ከኢትዮጵያ ጋር ያላትን ትብብሯን እንደምታጠናክር ገልፀዋል።   

በሰው ኃይል ልማት ትብብር ኢትዮጵያ የታንዛኒያን ሙያተኞች በማሰልጠን ትልቅ አስተዋጽዖ እያደረገች መሆኑንም ጠቁመዋል።

ኢትዮጵያ በምስራቅ አፍሪካ ሰላምና መረጋጋት እንዲመጣ ትልቅ ሚና እየተጫወተች መሆኗን ሚኒስትሯ ገልፀዋል።

የሁለቱን አገራት የሰላምና ጸጥታ ትብብር መስክ ወደ ላቀ ደረጃ ለማድረስ ታንዛኒያ በቁርጠኝነት እንደምትሰራ ተናግረዋል።

ሚኒስትሯ ከመከላከያ ሚኒስትር ኢንጂነር አይሻ መሀመድ ጋር በዚህ ሳምንት መወያየታቸው ይታወሳል።  

 

 

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም