ቀጥታ፡

የፌዴራል ቴክኒክና ሙያ ሥልጠና ኢንስቲትዩት አዳዲስ የፈጠራ ኃሳብ ያላቸው ዜጎች ለመደገፍ እየሰራ ነው

አዲስ አበባ፤ ሰኔ 1/2016(ኢዜአ)፡- የፌዴራል ቴክኒክና ሙያ ሥልጠና ኢንስቲትዩት አዳዲስ የፈጠራ ኃሳብ ያላቸው ዜጎች ለመደገፍ እየሰራ መሆኑን ገለጸ። 

ኢንስቲትዩቱ በቴክኒክና ሙያ ዘርፍ ለሚማሩ ተማሪዎች፣ መምህራንና አመራሮች ሥልጠና እየሰጠ ይገኛል። 

የኢንስቲትዩቱ ዋና ዳይሬክተር ብሩክ ከድር (ዶ/ር) ተቋሙ በሚሰጠው የአቅም ግንባታ ሥልጠና ለአገር ውስጥና ዓለም አቀፍ ገበያ ፍላጎት የሚመጥኑ ብቁ ሰልጣኞችን በማፍራት ላይ እንደሚገኝ ለኢዜአ ገልፀዋል።

በዚህም በ2016 በጀት ሥልጠና የወሰዱ አዳዲስ ኢንተርፕራይዞች ወደ ሥራ መግባታቸውንና በኢንተርፕራይዞቹ ሥር የሚገኙ ዜጎች በሥራቸው ላይ የንግድ እሳቤ እንዲላበሱ የተግባር ልምድ መቅሰማቸውን አመልክተዋል።

ሥልጠናው ኢንተርፕራይዞቹ የሥራ ገበያው የሚፈልገውን ብቁ ባለሙያ እንዲያፈሩ የሚያስችል መሆኑን ጠቅሰው፤ በቀጣይም የአቅም ግንባታ ድጋፉ ተጠናክሮ እንደሚቀጥል ተናግረዋል።

በሌላ በኩል በኢንስቲትዩቱ የክህሎት ማበልጸጊያ ማዕከል ከመላው አገሪቱ ክፍሎች የተመለመሉ ከ350 በላይ ልዩ ብቃት ያላቸው የፈጠራ ባለሙያዎች በክረምት መርሃ-ግብር ሥልጠና እየወሰዱ መሆኑን ነው ዋና ዳይሬክተሩ የጠቆሙት።

ሰልጣኞችም ተኪ ምርትን የሚያመርቱ ኢንተርፕራይዞችን እንዲያቋቋሙ የሚያስችል ድጋፍ እየተደረገላቸው መሆኑን አመልክተዋል።

የፌዴራል ቴክኒክና ሙያ ሥልጠና ኢንስቲትዩት የኢንዱስትሪ ሊንኬጅ ዳይሬክተር የማነ ዘሚካኤል(ዶ/ር) በበኩላቸው፤ ኢንስቲትዩቱ የሰው ኃይልና ተቋማዊ የአደረጃጀት ማሻሻያዎችን እያደረገ እንደሚገኝ ገልፀዋል።


 

ማሻሻያዎቹ ብቁና ተወዳዳሪ የሆነ እንዲሁም በዓለም አቀፍ ደረጃ ተቀባይነት ማግኘት የሚችል የሰው ኃይል ለማፍራት እንደሚያስችል አመልክተዋል።

በተጨማሪም ኢንተርፕራይዞቹ ከኢንዱስትሪዎች ጋር ትስስር እንዲፈጠርላቸው በማድረግ የተግባር ልምድ እያገኙ መሆኑን ተናግረዋል።

የቴክኒክና ሙያ ማሰልጠኛ ተቋማት ለአገራዊ ልማት በመካከለኛና ዝቅተኛ ደረጃ የሰለጠነ የሰው ኃይል በማቅረብ ላይ ይገኛሉ።

 

 

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም