ቀጥታ፡

የተሻሻሉ የዶሮ ዝርያዎች አቅርቦትን በማሳደግ ምርታማነትን ለመጨመር እየተሰራ ነው

አዲስ አበባ፤ ሰኔ 01/2016 (ኢዜአ)፡- ለቅድመ-ወላጅ ዶሮ እርባታ የሚያስፈልገውን የመሠረተ-ልማት ግንባታን በማጠናቀቅ እስከ ቀጣዩ ዓመት ታኅሳስ ድረስ የጫጩት ሥርጭት እንደሚጀመር የግብርና ሚኒስቴር ገለጸ። 

የሌማት ትሩፋት የእንስሳት ዘርፉን ምርትና ምርታማነት በመጨመር የሥርዓተ-ምግብ ሽግግር ለማምጣት፣ ሰፊ የሥራ ዕድልን ለመፍጠርና የውጭ ንግድን ለማስፋፋት በተመረጡ የወተት፣ የእንቁላል፣ የዶሮ፣ የማርና ዓሳ ምርታማነትን ለማሳደግ እየተተገበረ ይገኛል።

በዝርያ ማሻሻልና ግብዓት አቅርቦት ላይ በልዩ ትኩረት እየተሰራ ሲሆን፤ የአንድ ቀን ጫጩት አቅርቦትን ለማሳለጥ ቅድመ -ወላጅ ዶሮ መሠረተ-ልማት ግንባታ ከግል ባለኃብት ጋር በመተባበር መገንባት ተጀምሯል። 

ከውጭ የሚመጣውን መሥራች ዘር በአገር ውስጥ እንዲቀርብ ለማድረግ አቅም እየተገነባ በመሆኑ የተሻሻሉ የዶሮ ዝርያዎች አቅርቦትን በማሳደግ ምርታማነትን ለመጨመር እየተሰራ ነው። 

የግብርና ሚኒስትር ዴኤታ ፍቅሩ ረጋሳ (ዶ/ር) ለኢዜአ እንዳሉት፤ ከዚህ ቀደም የግራንድ ፓረንት (ቅድመ- ወላጅ ዶሮ) በየጊዜው ከውጭ ሲገባ በመቆየቱ ለግዥው የውጭ ምንዛሬ ከማስፈለጉ በተጨማሪ የበሽታ ሥጋት አለበት።


 

የግራንድ ፓረንት የሚያስገባው ባለኃብት ቁጥር አነስተኛ በመሆኑ በአገር ውስጥ ካለው ፍላጎት ጋር ያልተመጣጠነ እንደሆነም ነው ያስረዱት።

የሌማት ትሩፋት ያለበት ደረጃ ሲገመገም እንደ ችግር የታየው ኢትዮጵያ የግራንድ ፓረንት ስቶክ (ቅድመ- ወላጅ ዶሮ) ስለሌላት መንግሥት በዘርፉ የተሰማሩ ባለኃብቶች የእነዚህን የዶሮ ዝርያ ወደ አገር ውስጥ እንዲያስገባ ሥምምነት ላይ እንደተደረሰ ተናግረዋል።

ለቅድመ-ወላጅ ዶሮ እርባታ የሚስፈልገው ተገጣጣሚ ቤት ሥራ መጀመሩን አንስተው፤ ሥራውን በማጠናቀቅ የዶሮ ዝርያ የማምጣቱ ተግባር በዚህ ዓመት የሚጠናቀቅ እንደሆነ አንስተዋል።

እስከ ታኅሳስ 2017 ዓ.ም ድረስ የቅድመ-ወላጅ ጫጩቶች ሥርጭት እንደሚጀመር አንስተው፤ ይህም የአገሪቱን ፍላጎት ከማሟላት ባለፈ ወደ ውጭ አገራት በመላክ የውጭ ምንዛሬ ለማግኘት የሚያስችል እንደሆነ ነው የገለፁት።    

ኬንያ፣ ሱዳንና ታንዛኒያ የቅድመ-ወላጅ ዶሮ እንዳላቸው ጠቅሰው፤ ኢትዮጵያ ትልቅ ሕዝብና ለዶሮ እርባታ ምቹ ሁኔታ እያላት ሥራው ያለመጀመሩ ትልቅ ስብራታችን ነው ብለዋል።

የቅድመ-ወላጅ ዶሮ እርባታ ፕሮጀክቱ ከሦስት ዓመት በኋላ ከውጭ የሚገባውን ዝርያ የሚያስቀር መሆኑንም ነው ያነሱት።

የሚድሮክ ኢንቨስትመንት ግሩፕ የአግሮ ክላስተር ምክትል ዋና ሥራ አስፈጻሚ ፈለቀ ታደሰ በበኩላቸው፤ በጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ (ዶ/ር) አነሳሽነት የቅድመ-ወላጅ ዶሮ ፕሮጀክት ለሚድሮክ መሰጠቱን ተከተሎ የዳሰሳ ጥናት በማካሄድ ሥራው ተጀምሯል ብለዋል።

 

በአገሪቱ የሚያስፈልገው ለሥጋም ለእንቁላልም የሚሆኑ የጥመርታ ዝርያ መሆን እንዳለበት ከግብርና ሚኒስቴር ጋር በመግባባት ሀንጋሪ አገር ከሚገኝ "ባቡሊና" ከተሰኘ ድርጅት ዝርያ ለማግኘት የሚያስችል ሥምምነት መደረጉን ተናግረዋል።

እንዲሁም "አግሮ ፊድ" ከተሰኘ የሀንጋሪ ድርጅት ጋር የመኖ አቅርቦት ለማግኘት የሚያስችል ሥምምነት መደረጉን ጠቅሰዋል።

የፕሮጀክቱ መሠረተ-ልማት ግንባታ ሻሎ እርሻ ላይ እየተከናወነ መሆኑን ተናግረው፤ እስከ ነሐሴ መጀመሪያ ድረስ ግንባታው ተጠናቆ ዝርያውን የማምጣት ሥራ እንደሚሰራ ገልፀዋል።

ንቁና በአዕምሮ የበለፀገ ዜጋ ለማፍራት ገንቢ ምግብ ወሳኝ በመሆኑ ይህ ፕሮጀክት ውጤታማ እንዲሆን ሁሉም የበኩሉን ሚና እንዲወጣም ጠይቀዋል።

  

 

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም