አርማወር ሐንሰን የምርምር ኢንስቲትዩት ምርምሮች ከኢትዮጵያ አልፎ ለዓለም ጤና መሻሻል አዎንታዊ አስተዋጽዖ እያበረከቱ ነው

አዲስ አበባ፤ ሰኔ 1/2016(ኢዜአ)፦አርማወር ሐንሰን የምርምር ኢንስቲትዩት በምርምር የሚያወጣቸው ምክረ-ኃሳቦች ከኢትዮጵያ አልፎ ለዓለም ጤና መሻሻል አዎንታዊ አስተዋጽዖ እያበረከቱ መሆኑ ተገለጸ። 

ኢንስቲትዩቱ 54ኛ ዓመት የምስረታ በዓሉን በማስመልከት ለሁለት ቀናት ያዘጋጀው የጉብኝትና ግንዛቤ ማስጨበጫ መርኃ-ግብር በትላንትናው ዕለት ተጠናቋል።       

መርኃ-ግብሩ ኢንስቲትዩቱ በቆይታው ያበረከተውን አስተዋጽዖ ለማስተዋወቅ ያለመ ሲሆን፤ በመርኃ-ግብሩ ላይ የፌደራልና የክልል ኮሙኒኬሽን ባለሙያዎች፣ ጋዜጠኞች፣ የጤናው ዘርፍ ባለድርሻ አካላት ተሳትፈዋል።       

የአርማወር ሐንሰን ምርምር ኢንስቲትዩት ዋና ዳይሬክተር ፕሮፌሰር አፈወርቅ ካሱ በዚሁ ጊዜ እንደተናገሩት፤ ኢንስቲትዩቱ በምርምር የሚያወጣቸው ምክረ-ኃሳቦች ለፖሊሲ አውጪዎች፣ የጤና ባለሙያዎችና ተቋማት ግብዓት እየሆኑ ነው።    

ለአብነትም መድኃኒት የተላመደ ቲቢ የሕክምና ጊዜ ከ24 ወር ወደ 9 ወር ዝቅ እንዲል ማድረግ የሚያስችል ውጤት በምርምር መገኘቱን ጠቅሰዋል።       

መድኃኒት የተላመደ ቲቢ ላይ በተደረገ ሁለተኛ ዙር ምርምርም የሕክምና ጊዜው ከ9 ወር ወደ 6 ወር ዝቅ ሊል እንደሚችል ጠቋሚ ውጤት መገኘቱን ጠቁመው፤ ለአጠቃላይ ሕክምናው መሻሻል ትልቅ እርምጃ ነው ሲሉም ተናግረዋል።     


 

የምርምር ውጤቱ "ላንሴት" በተሰኘ ዓለም አቀፍ ጆርናል ላይ የታተመ ሲሆን፤ የዓለም የጤና ድርጅት መድኃኒት የተላመደ ቲቢን በተመለከተ ቀድሞ የነበረውን ፕሮቶኮል መቀየር ያስቻለ ውጤት ተገኝቶበታል ነው ያሉት።  

ፕሮፌሰር አፈወርቅ እንዳሉት፤ ኢንስቲትዩቱ የሚያወጣቸው የምርምር ምክረ-ኃሳቦች ከኢትዮጵያ አልፎ ለዓለም ጤና መሻሻል አዎንታዊ አስተዋጽዖ እያበረከቱ ነው። 

እንደ ዋና ዳይሬክተሩ ገለጻ፤ ኢንስቲትዩቱ በምርምር ያገኛቸው ውጤቶች በዓለም አቀፍ ደረጃ እውቅና ባላቸው ከ1 ሺህ በላይ መጽሔቶች ላይ መታተማቸውንም አብራርተዋል።  

የኤች አይ ቪ እና ጉበት በሽታዎችን ጨምሮ በርካታ ተላላፊና ተላላፊ ያልሆኑ በሽታዎች ላይም እንዲሁ ምርምሮች ተጠናክረው ቀጥለዋል ነው ያሉት።        

ከክትባት ጋር በተያያዘም የማጅራት ገትር፣ ኒሞኒያና ሌሎች በሽታዎች ላይ ክትባት እንዲዘጋጅ በማድረግ ለጤናው ዘርፍ እድገትና ጥራት ኢንስቲትዩቱ የድርሻውን እየተወጣ ነው ብለዋል።

በጤና ሚኒስቴር የሕዝብ ግንኙነትና ኮሙኒኬሽን ሥራ አስፈጻሚ ዶክተር ተገኔ ረጋሳ በበኩላቸው፤ ኢንስቲትዩቱ በኢትዮጵያ ጤና ሥርዓት ውስጥ ፋይዳቸው የላቀ ምርምሮች እያካሄደ መሆኑን አንስተዋል።       


 

ይሁን እንጂ የምርምር ውጤቶችን በማስተዋወቅ ረገድ የሚዲያና ኮሙኒኬሽን ባለሙያዎችና ባለድርሻ አካላት በሚጠበቅባቸው ደረጃ እየሰሩ እንዳልሆነ አንስተዋል።  

በተለይም መገናኛ ብዙኃን ከምርምር ተቋማትና ባለሙያዎች ጋር ተቀራርበው በመሥራት በዚህ በኩል የሚስተዋለውን ክፍተት ለመሙላት መሥራት እንደሚጠበቅባቸው አስገንዝበዋል።

የጤና ሚኒስቴር ተመራማሪዎች በማበረታታት ምርምሮች እንዲጠናከሩ የሚያስችል ሥርዓት መዘርጋቱንም  ገልፀዋል።       

አርማወር ሐንሰን የምርምር ኢንስቲትዩት በ1962 ዓ.ም መመስረቱን መረጃዎች ያመለክታሉ። 

 

 

 

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም