ቀጥታ፡

የሳዑዲ አረቢያ ባለኃብቶች በኢትዮጵያ በተለያዩ የኢንቨስትመንት ዘርፎች መሰማራት እንደሚፈልጉ ገለጹ

አዲስ አበባ፤ ሰኔ 1/2016(ኢዜአ)፦ የሳዑዲ አረቢያ ባለኃብቶች በኢትዮጵያ በግብርና፣ ምግብ ማቀነባበሪያና በግንባታ በኢንቨስትመንት ዘርፎች የመሰማራት ፍላጎት እንዳላቸው ተናገሩ።

ከቀናት በፊት በሳዑዲ አረቢያ የንግድ ምክር ቤት ፌዴሬሽን የተመራ ልዑካን ቡድን አዲስ አበባ መግባቱ ይታወሳል።

ይህንንም ተከትሎ የኢትዮ-ሳዑዲ የንግድና ኢንቨስትመንት ፎረም በአዲስ አበባ ተካሂዷል።

ለልዑክ ቡድኑ በኢትዮጵያ የኢንቨስትመንት አማራጮችና ምቹ ሁኔታዎች ላይ በሚመለከታቸው አካላት ገለፃ ተደርጎላቸዋል።

በመድረኩ በኢትዮጵያ የንግድና ዘርፍ ማኅበራት ምክር ቤት እና በሳዑዲ አረቢያ አቻው መካከል የመግባቢያ ሥምምነት ተፈርሟል።

ልዑክ ቡድኑ በተግባር የአምራች ኢንዱስትሪው ያለበትን የሥራ እንቅስቃሴም ተዘዋውሮ የጎበኘ ሲሆን፤ ከጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ (ዶ/ር) ጋር ተገናኝቶ ውይይት አድርጓል።

ከልዑክ ቡድኑ መካከል በማዳበሪያና በእንስሳት መኖ፣ በግንባታና በምግብ ማቀነባበሪያ ኢንቨስትመንት ዘርፍ የተሰማሩ ባለኃብቶች በኢትዮጵያ ሰፊ የኢንቨስትመንት አማራጭ እንዳለ መረዳታቸውን ለኢዜአ ገልፀዋል።

ለኢንቨስትመንት የሚሰጡ ማበረታቻዎች፣ ምቹ የአየር ጸባይ፣ አምራች የሰው ኃይል፣ የገበያ አማራጮች ለኢንቨስትመንት ተመራጭ መሆኗን እንደተገነዘቡ ተናግረዋል።

በመሆኑም ያለውን ሰፊ የኢንቨስትመንት አማራጭ በመጠቀም በኢትዮጵያ መዋዕለ-ነዋያቸውን ለማፍሰስ ፍላጎት እንዳላቸው ነው የገለጹት።

በምግብ ማቀነባበሪያ ኢንቨስትመንት ዘርፍ የተሰማሩት ኢንጂነር መሃመድ ቢን አሕመድ፤ ኢትዮጵያ በእንስሳት እርባታ፣ በምግብ ማቀነባበሪያ ያላትን ትልቅ አቅም ለመጠቀም እንደሚፈልጉ ተናግረዋል።

በግንባታ ዘርፍ የተሰማሩት ሱሊማን አልአሞሪ በተመሳሳይ በኢትዮጵያ በግንባታ ዘርፍ ለመሰማራት ፍላጎት እንዳላቸው ጠቁመዋል።

በኢትዮጵያ ያለውን የኢንቨስትመንት አማራጭ ለመጠቀም እንደሚሰሩ የገለጹት ደግሞ በግንባታ ዘርፍ የተሰማሩት ኢንጂነር ሳሊህ ቢን አሕመድ ናቸው።


 

ኢትዮጵያና ሳዑዲ አረቢያ በሕዝብ ለሕዝብና በባህል ታሪካዊና ጠንካራ ግንኙነት ያላቸው ሲሆን፤ በንግድና ኢንቨስትመንት ያላቸውን አጋርነት ለማጠናከር እየተሰራ ነው።

 

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም