''ሰላም ለሁሉም፤ ሁሉም ለሰላም'' የ5 ኪሎ ሜትር የጎዳና ላይ ሩጫ ውድድር ሰኔ 23 ቀን 2016 ዓ.ም ይካሄዳል - ኢዜአ አማርኛ
''ሰላም ለሁሉም፤ ሁሉም ለሰላም'' የ5 ኪሎ ሜትር የጎዳና ላይ ሩጫ ውድድር ሰኔ 23 ቀን 2016 ዓ.ም ይካሄዳል
አዲስ አበባ፤ ሰኔ 1/2016(ኢዜአ)፦ አገር አቀፉ ''ሰላም ለሁሉም፤ ሁሉም ለሰላም'' የ5 ኪሎ ሜትር የጎዳና ላይ የሩጫ ውድድር ሰኔ 23 ቀን 2016 ዓ.ም ሊያካሂድ መሆኑን የሰላም ሚኒስቴር ገለጸ።
የሰላም የሩጫ ውድድሩ የሰላም ሚኒስቴር፣ የባህልና ስፖርት ሚኒስቴር፣ የኢትዮጵያ አትሌቲክስ ፌዴሬሽን፣ የታላቁ ሩጫ በኢትዮጵያን ጨምሮ የክልል የባህልና ስፖርት ቢሮዎች ጋር በመተባበር የሚካሄድ ነው ተብሏል።
የማስጀመሪያ መርኃ-ግብሩ በሰላም ሚኒስቴር አዘጋጅነት በአዲስ አበባ የሚካሄድ ሲሆን፤ በከተማ አስተዳደሮችና በክልል ከተሞች በተመሳሳይ ጊዜ በሚካሄደው በዚህ የሩጫ ዝግጅት ታዋቂ አትሌቶችን ጨምሮ በርካታ ሰዎች እንደሚሳተፉበት ተገልጿል።
ውድድሩን አስመልክቶ ዛሬ በተዘጋጀው መርኃ ግብር፤ የሰላም ሚኒስትር ዴኤታ ከይረዲን ተዘራ (ዶ/ር)፤ የሩጫ ውድድሩ ዜጎችን በማሳተፍ ብሔራዊ መግባባት ለመፍጠር፣ አብሮነትን በማጠናከርና ዘላቂ ሰላምን ለመገንባት ያለመ መሆኑን ተናግረዋል።
ይህም ብቻ ሳይሆን መንግሥት ለሰላም ያለውን ቁርጠኝነት ለማሳየት የተዘጋጀ እንደሆነም ገልፀዋል።
በሩጫ ውድድሩ ዜጎች የእርስበርስ ግንኙነትንና ሕብረ-ብሔራዊ አንድነታቸውን በማጠናከር ለሰላም ግንባታ የበኩላቸውን እንዲወጡ ለማድረግ ያለመ መሆኑንም ጠቁመዋል።
ስፖርት የአንድነት፣ የፍቅርና የአብሮነት እሴት የሚንፀባረቅበት መሆኑን በመግለፅ፤ ሰላምን ለመገንባት ለሚደረገው ጥረትም ወሳኝ ሚና እንዳለውም ነው የጠቆሙት።