የኢትዮጵያ ልዑካን ቡድን በ3ኛው የብሪክስ አባል ሀገራት ተወካዮች ስብሰባ ላይ እየተሳተፈ ይገኛል - ኢዜአ አማርኛ
የኢትዮጵያ ልዑካን ቡድን በ3ኛው የብሪክስ አባል ሀገራት ተወካዮች ስብሰባ ላይ እየተሳተፈ ይገኛል
አዲስ አበባ፤ግንቦት 30/2016(ኢዜአ)፦ የኢትዮጵያ ብሔራዊ ባንክ ገዥ እና በብሪክስ የኢትዮጵያ ዋና ተወካይ አቶ ማሞ እስመልዓለም ምህረቱ የሚመራ የልዑካን ቡድን ዛሬ በሩሲያ በጀመረው 3ኛው የብሪክስ የአባል ሀገራት ተወካዮች ስብሰባ ላይ እየተሳተፈ ይገኛል።
አቶ ማሞ በስብሰባው ላይ ባደረጉት ንግግር በተለዋዋጭና ሊተነበይ በማይቻል የአለም ኢኮኖሚና ፖለቲካ ምኅዳር ዉስጥ ብሪክስ ሀገራትን እና ሃብቶችን በማሰባሰብ ዓለም አቀፍ ተግዳሮቶችን በአጋርነት መንፈስ ለመቅረፍ አረጋጊ ኃይል ሆኖ ሊያገለግል እንደሚችል ጠቅሰዋል።
አክለውም፣ ኢትዮጵያ የብሪክስ ብሔራዊ ተሳትፎ ስትራቴጂን በብሔራዊ የሚኒስትሮች አስተባባሪ ኮሚቴ ማፅደቋንና ወደ ብሪክስ ማዕቀፍ በተሳለጠ ሁኔታ መግባቷን ለማረጋገጥ የተወሰዱ እርምጃዎችን አብራርተዋል።
በብሪክስ አባል አገራት መካከል በንግድ፣ ኢንቨስትመንት ፣ ቱሪስት ፍሰትና ሌሎች መስኮች ያለውን የኢኮኖሚ ግንኙነት ማሳደግ እንደሚገባና የልማት ፋይናንስን በመጨመር የአካታች እና ዘላቂ ልማትን የመደገፍ አስፈላጊነትንም ገልጸዋል።
አዲሱ የልማት ባንክ ቅድሚያ የሚሰጣቸው ጉዳዮች ከኢትዮጵያ የልማት ትልሞች ጋር የተጣጣሙ በመሆናቸው ኢትዮጵያ በተቻለ ፍጥነት ወደ ባንኩ ትቀላቀላለች ብለው እንደሚጠብቁም ተናግረዋል።
ስብሰባው ከሰኔ 3 -4 ቀን 2016 ዓ.ም ለሚካሄደው የብሪክስ አባል ሀገራት የውጭ ጉዳይ ሚኒስትሮች ስብሰባ ግብዓት የሚሆኑ የተለያዩ አጀንዳዎች ላይ መምከሩን ከውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር የተገኘው መረጃ ያመለክታል።