የክልሉን ሁለንተናዊ ለውጥ እውን ለማድረግ በሳይንስና ኢኖቬሽን ቴክኖሎጂ ላይ ትኩረት ተደርጓል

ሆሳዕና ፤ ግንቦት 30/2016 (ኢዜአ)፦  በማዕከላዊ ኢትዮጵያ ክልል ሁለንተናዊ ለውጥ ለማምጣት በሳይንስና ኢኖቬሽን ቴክኖሎጂ ላይ ትኩረት ተሰጥቶ እየተሰራ መሆኑን የክልሉ ምክትል ርዕሰ መስተዳድርና የማህበራዊ ክላስተር አስተባባሪ አቶ አንተነህ ፈቃዱ ገለጹ።

"ማዕከላዊ ኢትዮጵያን የሳይንስ፣ የኢኖቬሽንና የቴክኖሎጂ ማዕከል እናድርግ" በሚል መሪ ሃሳብ የተዘጋጀ የፓናል ውይይት በሆሳዕና ከተማ እየተካሄደ ነው።

አቶ አንተነህ በዚህ ወቅት እንደተናገሩት፤ በክልሉ ሁለንተናዊ ለውጥን ለማምጣትና ዘላቂነቱን ለማረጋገጥ የኢኖቬሽንና ቴክኖሎጂ ስራዎችን መደገፍ ትኩረት የተሰጠው ጉዳይ ነው።

''የኢኖቬሽን፣ ቴክኖሎጂና የፈጠራ ስራዎች መስፋፋት የልማትና የለውጥ ስራዎችን በጥራትና በብዛት ተደራሽ እንዲሆኑ እንዲሁም የጊዜና ጉልበት ብክነትን በማስቀረት ተጠቃሚ የሚያደርጉ ናቸው'' ብለዋል። 

ዘመኑ ከደረሰበት ጋር ራስን እያስታረቁ መሄድ ወሳኝ እርምጃ ነው ያሉት አቶ አንተነህ በክልሉ የሚከናወኑ ተግባራት በቴክኖሎጂ የታገዙ እንዲሆኑ ማድረግ ተገቢ መሆኑን አንስተዋል።

ለዚህም በክልሉ በየአካባቢው እንዲሁም በምርምር ተቋማት የሚታዩ የቴክኖሎጂና የፈጠራ ስራ ውጤቶች እየሰፉ እንዲሄዱና የማህበረሰብን ችግር በተጨባጭ እንዲፈቱ ለማስቻል እንደሚሰራም አመልክተዋል።

አዳዲስ ሃሳቦችን በማስረፅ ተግባራዊ እንዲሆኑ ትኩረት መደረጉን አንስተው ከመጪው ጊዜ ሰው ሰራሽና ተፈጥሯዊ ችግሮች ለመላቀቅ በዘርፉ ላይ ትኩረት ሰጥቶ መስራት ይገባልም ብለዋል።


 

በዚህ ዘርፍ የተሰማሩትን በማብቃትና በማበረታታት ባለድርሻ አካላት የበኩላቸውን አስተዋጽኦ እንዲያበረክቱም አቶ አንተነህ ጥሪ አቅርበዋል።

"በፈጠራ ስራ የዳበረ ትውልድ ለብልፅግና" በሚል መሪ ሃሳብ ከ100 በላይ የፈጠራ ስራዎች የቀረቡበት ክልል አቀፍ የፈጠራ ስራዎች ውድድርና አውደ ርዕይ በትናንትናው ዕለት መከፈቱ ይታወሳል።

 

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም