በሜጀር ጀነራል ተስፋዬ አያሌው የተጻፈው "የጀግንነት ሥነ ልቦና" የወታደራዊ ሥነ ልቦና መጽሐፍ ተመረቀ - ኢዜአ አማርኛ
በሜጀር ጀነራል ተስፋዬ አያሌው የተጻፈው "የጀግንነት ሥነ ልቦና" የወታደራዊ ሥነ ልቦና መጽሐፍ ተመረቀ
አዲስ አበባ፤ ግንቦት 30/2016 (ኢዜአ)፦ በሜጀር ጀነራል ተስፋዬ አያሌው የተጻፈው "የጀግንነት ሥነ ልቦና" የወታደራዊ ሥነ ልቦና መጽሐፍ ተመረቀ፡፡
በመጽሐፉ ምርቃት ላይ የሶማሌ ክልል ርዕሰ መስተዳድር ሙስጠፌ መሀመድ፣ የመከላከያ ሚኒስትር ዴኤታ ማርታ ሉዊጂ፣ የመስኖና ቆላማ አካባቢዎች ሚኒስትር ዶክተር አብርሀም በላይ፣ የኢትዮጵያ ፌደራል ፖሊስ ኮሚሽነር ጀነራል ደመላሽ ገብረሚካኤል፣ የመከላከያ ሰራዊት ከፍተኛ መኮንኖች፣ የመንግስት የሥራ ኃላፊዎች፣ ታዋቂ ግለሰቦች እና ሌሎች ጥሪ የተደረገላቸው እንግዶች ተገኝተዋል።
ሜጀር ጀነራል ተስፋዬ አያሌው ከመሰረታዊ ወታደርነት እስከ ከፍተኛ ጀነራል መኮንንነት በታማኝነትና ቅንነት በተለያዩ ኃላፊነቶች እያገለገሉ ይገኛሉ።
ጀነራል መኮንኑ በማኔጅመንት ኢንፎርሜሽን ሲስተም የመጀመሪያ ዲግሪ፣ እንዲሁም በሊደርሺፕና መልካም አስተዳደር የሁለተኛ ዲግሪ አላቸው።
በስዊድን የተባበሩት መንግስታት ድርጅት የወታደራዊ ስታፍን ጨምሮ በተለያዩ ሀገራት ከፍተኛ የአመራር ኮርስ ወስደዋል።
በተባበሩት መንግስታት ድርጅት የዳርፉር ሰላም ማስከበር ሴክተር ሶስት የዘመቻ ኃላፊ፣ የምስራቅ አፍሪካ ተጠባባቂ ሀይል የዘመቻና የመረጃ ኃላፊ በመሆን አገልግለዋል።
ለ30 ዓመታት በዘለቀው ከተዋጊነት እስከ አዋጊነት የወታደራዊ ሀላፊነታቸው ለሀገራቸው ባበረከቱት አስተዋጽኦ ምርጥ የዘመቻ መኮንን ሜዳሊያ ሽልማት ተበርክቶላቸዋል።
በ11 ምዕራፎች እና 360 ገፆች የተቀነበበው የጀግንነት ሥነ ልቦና መጽሐፍ በአማርኛ፣ ኦሮምኛ፣ ሶማሊኛና እንግሊዘኛ ቋንቋዎች የተዘጋጀ ሲሆን አቀራረቡም ከታሪካዊ ሥነ ልቡና ዳሰሳ እስከ ንድፈ ሀሳባዊ መርሆዎች የወታደራዊ ሥነ ልቡናን አተገባበር ይተነትናል።
ደራሲው ሜጀር ጀነራል ተስፋዬ አያሌው መጽሐፉን ለማዘጋጀት 42 የአማርኛና እንግሊዝኛ ማጣቀሻ መጽሐፍት ተጠቅመዋል።
ወታደራዊ፣ ሲቪልና ማህበራዊ ጀግንነት ምን እንደሆኑ በመተንተን ኢትዮጵያ ሁሉንም አይነት የጀግንነት ባህርይ ያላት መሆኗንም ይገልጻል።
መጽሐፉ ከወታደራዊ ሀይሎች በተጨማሪ ሁሉም የማህበረሰብ ክፍል ሊያነበውና የህይወቱ መርህ ሊያደርገው የሚገባ ነው።
የጀግንነት ስነ ልቦና መጽሐፍ በቻይናው ጀነራልና ስትራቴጂስት ከተፃፈው "Art of war" ጋር የሚስተካከል ድንቅ መጽሐፍ መሆኑም ተገልጿል።
መጽሐፉ የሥነ ልቦና ጦርነትን የኢትዮጵያ ወታደራዊ አደረጃጀት በምን መልኩ መጠናከር እንዳለበት ምክረ ሀሳብም ያቀርባል።
የወታደራዊ ስነልቦና ምንነት፣ ወታደራዊ ጀግንነት፣ ወታደራዊ ሳይንስ፣ የጦርነት ሥነ ልቦና ዝግጅት፣ የወታደራዊ አመራር ፅንሰ ሀሳብና የተግባር አመራር በወታደራዊ ስልጠና ላይ ቅሬታን የማስወገድ ስልቶችና ወታደራዊ ግምገማ ምን እንደሚመስል በመጽሐፉ በዝርዝር ቀርበዋል።
በአጠቃላይ ከውጊያ በፊት፣ በውጊያ ወቅትና በኋላ ሊኖር የሚገባውን የጀግንነት ሥነ ልቦና ዝግጅትና ወኔ በዝርዝር ያስረዳል።