በኢኮኖሚ ዲፕሎማሲ እየተከናወኑ ያሉ ተግባራት ኢትዮጵያን ተመራጭ የንግድና ኢንቨስትመንት መዳረሻ እያደረጋት ይገኛል - የውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር - ኢዜአ አማርኛ
በኢኮኖሚ ዲፕሎማሲ እየተከናወኑ ያሉ ተግባራት ኢትዮጵያን ተመራጭ የንግድና ኢንቨስትመንት መዳረሻ እያደረጋት ይገኛል - የውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር
አዲስ አበባ፤ ግንቦት 30/2016(ኢዜአ)፦ በኢኮኖሚ ዲፕሎማሲ እየተከናወኑ ያሉ ተግባራት ኢትዮጵያን ተመራጭ የንግድና ኢንቨስትመንት መዳረሻ እያደረጋት መሆኑን የውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር አስታወቀ።
ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ(ዶ/ር) እና ልዑካቸው በኮሪያ ሪፐብሊክ እና ሲንጋፖር በነበራቸው ቆይታ ውጤታማ የኢኮኖሚ ዲፕሎማሲ ማከናወናቸው ተገልጿል።
የውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር ቃል አቀባይ አምባሳደር ነብዩ ተድላ፤ በሳምንቱ የተከናወኑ ዋና ዋና የዲፕሎማሲ ተግባራትንና ቀጣይ ስራዎችን አስመልክቶ ለመገናኛ ብዙኃን መግለጫ ሰጥተዋል።
በመግለጫቸውም የጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ(ዶ/ር) የኮሪያ ሪፐብሊክ እና ሲንጋፖር ቆይታ፣ የሳዑዲ አረቢያና ፓኪስታን የንግድና ኢንቨስትመንት ልዑክ የኢትዮጵያ ጉብኝትና ሌሎች ጉዳዮችን አብራርተዋል።
ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ(ዶ/ር) በኮሪያ ሪፐብሊክ እና ሲንጋፖር ቆይታቸው ውጤታማ የኢኮኖሚ ዲፕሎማሲ ማከናወናቸውን አስታውቀዋል።
በዚህም ኢትዮጵያና ኮሪያ ሪፐብሊክ በአራት ዓመታት የሚተገበር የአንድ ቢሊዮን የአሜሪካን ዶላር የልማት ፋይናንስ ትብብር ስምምነት በመፈራረም የሀገራቱን ቀደምት ወዳጅነት ለማጠናከር መስማማታቸውን ገልጸዋል።
በኢትዮጵያ የፌዴራል የሥነ ምግባር እና ፀረ ሙስና ኮሚሽን እና በኮሪያ ሪፐብሊክ ፀረ ሙስና እና ሲቪል መብቶች ኮሚሽን መካከል የመግባቢያ ሰነድ መፈረሙንም እንዲሁ፡፡
የኮሪያ-አፍሪካ ጉባኤ መጠናቀቅ በኋላም ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ(ዶ/ር) በሲንጋፖር ያደረጉት ስኬታማ የስራ ጉብኝት የኢትዮ-ሲንጋፖርን ኢኮኖሚያዊ ትብብር የሚያጎለብት መሆኑን አስረድተዋል።
በጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ(ዶ/ር) የተመራው ልዑክ በሲንጋፖር በነበረው የሥራ ጉብኝት በዘመናዊ ከተማ፣ በግብርና፣ በአረንጓዴ ኢኮኖሚ እና በቱሪዝም ልማት መስኮች ልምድ መቅሰም ተችሏል ብለዋል።
የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር አምባሳደር ታዬ አጽቀስላሴ በሳዑዲ አረቢያ የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር ፈይሰል ቢን ፋርሃን አል-ሳዑድ ጋር በሁለትዮሽ ጉዳዮች ዙሪያ ስኬታማ ውይይት ማድረጋቸውንም አንስተዋል።
በተጨማሪም ሚኒስትሩ ተቀማጭነታቸውን አዲስ አበባ ካደረጉት የመንግስታቱ ድርጅት ረዳት ዋና ፀኃፊና የሰብዓዊ ዕርዳታ አስተባባሪ ራሚዝ አላክባሮቭ፣ በኢትዮጵያ የስፔንና ኳታር አምባሳደሮች ጋር መወያየታቸውን ጠቅሰዋል።
በሌላ በኩል የሳዑዲ አረቢያ ከፍተኛ የቢዝነስ ልዑክ በኢትዮጵያ ያደረገው ጉብኝት የሀገራቱን ታሪካዊ ዲፕሎማሲያዊ ግንኙነት በማጠናከር የንግድና ኢንቨስትመንት አማራጮችን ለማስፋት ዓላማ ያደረገ ነው ብለዋል።
የንግድና ኢንቨስትመንት ልዑኩ በአዲስ አበባ ያደረገው ጉብኝት ረጅም እድሜ ያስቆጠረውን የኢትዮ-ሳዑዲ ዲፕሎማሲን በማጠናከር የኢኮኖሚ፣ የፖለቲካና ጸጥታ ትብብርን የሚያሳድግ መሆኑን ገልጸዋል።
ልዑካን ቡድኑ በቆይታው በግብርና፣ በማዕድን፣ በኃይል እንዲሁም በቁልፍ የኢኮኖሚ መስኮች መሰማራት በሚችሉባቸው ጉዳዮች ዙሪያ ከመንግስት ከፍተኛ የሥራ ኃላፊዎች ጋር ውጤታማ ውይይት ማድረጉን አንስተዋል፡፡
ባለፉት ሁለት አስርት ዓመታት የሳዑዲ አረቢያ ባለሃብቶች በኢትዮጵያ 260 ቢሊዮን ብር በሚያወጡ ኢንቨስትመንቶች ላይ በመሰማራት ለ75 ሺህ ኢትዮጵያውያን የሥራ ዕድል መፍጠራቸውንም ተናግረዋል።
ከዚህ አኳያ የሳዑዲ አረቢያ ቢዝነስ ልዑክ የኢትዮጵያ ጉብኝት የንግድና ኢንቨስትመንት ትብብርን ይበልጥ ያሳድጋል ነው ያሉት፡፡
በተጨማሪ የፓኪስታን የንግድና ኢንቨስትመንት ልዑክ በኢትዮጵያ ለስድስት ቀናት ያደረገው ጉብኝት የሀገራቱን ኢኮኖሚያዊ ትስስር በማጎልበት ረገድ ሚናው የጎላ ነው ብለዋል፡፡
የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር ዴኤታ አምባሳደር ምስጋኑ አርጋ በተገኙበት በተርክዬ የተካሄደው የኢትዮ-ተርክዬ የንግድና ኢንቨስትመንት መድረክ ሌላኛው ስኬታማ የኢኮኖሚ ዲፕሎማሲ መሆኑንም ተናግረዋል።
በአጠቃላይ የሳዑዲ አረቢያና ፓኪስታን የቢዝነስ ልዑክ ጉብኝት እና በተርክዬ የተካሄደው የንግድና ኢንቨስትመንት የምክክር መድረክና ኤክስፖ የኢኮኖሚ ዲፕሎማሲ ስራ ውጤት ነው ብለዋል።
የኢኮኖሚ ዲፕሎማሲ ተግባራት የውጭ ቀጥታ ኢንቨስትመንትን በማነቃቃት ኢትዮጵያን ተመራጭ የንግድና ኢንቨስትመንት ሀገር እንድትሆን እያስቻላት መሆኑንም ነው የገለጹት።
ለደቡብ ሱዳን ዲፕሎማቶች በአዲስ አበባ የተሰጠው ስልጠናም የሁለቱን ሀገራት ወዳጅነት ወደ ላቀ ደረጃ የሚያሸጋግር መሆኑንም አስታውቀዋል።