ታሪክ አስታዋሽ፣ በወንድማማችነት የተመሰረተና ትብብርን ያፀና ዲፕሎማሲያዊ ጉዞ

ክቡር ጠቅላይ ሚንስትር ዐቢይ አሕመድ (ዶ/ር) በደቡብ ኮሪያ እና በሲንጋፖር የነበራቸው ቆይታ፣ ኢትዮጵያ ለጀመረችው የኢኮኖሚ ማሻሻያ፣ እድገት እና የለውጥ ጉዞ (ሪፎርም) ታላቅ አሻራ አኑሯል።

በሁለቱ ሀገራት የተደረገው ጉዞ አዳዲስ ልምዶች ለመቅሰም፣ የኢንቨስትመንት አማራጮችን ለማስተዋወቅ፣ ከሀገሮቹ ጋር አዳዲስ የትብብር እና የግንኙነት ማዕቀፍ ለመፍጠር እንዲሁም እያደገ ላለው ኢኮኖሚያችን ቀጣይነት የፋይናንስ ድጋፍ ለማስፋት ጭምር ያለመ ሲሆን ይህንኑም በተጨባጭ አሳክቷል።

ኮሪያና ሲንጋፖር ባለፉት ስልሳ እና ከዚያ በላይ ዓመታት እጅግ ዝቅተኛ ከሆነ የዕድገት ደረጃ ተነስተው አስደናቂ ማህበረ- ኢኮኖሚያዊ ዕድገት በማስመዝገብ ከዓለማችን የበለፀጉ ሀገራት ተርታ መሰለፍ የቻሉ ናቸው።

ለተፈጥሮ ሃብት ጥበቃ፣ ለሰብአዊ ሀብት ልማትና በኢኮኖሚያቸው ውስጥ የየሀገሮቻቸው መንግስታት የነበራቸው ወሳኝ ሚና፣ ለዕድገት እና ብልጽግናቸው ቀጣይነት የማይተካ ድርሻ አበርክቷል።


 

በዚህ ሂደት በየወቅቱ የነበሩ መሪዎቻቸው ባሳዩት ቁርጠኝነት እና በተከተሉት የኢኮኖሚ ፖሊስ ሀገራቱ የሚመሳሰሉ በመሆኑ ኢትዮጵያ ለጀመረችው የብልጽግና ጉዞ ጠቃሚ ልምድ የሚቀሰምባቸው ናቸው።

ይሁን እንጂ ሁለቱም ሀገራት ለዕድገት ዘርፎች በሰጡት ትኩረት እና ቅደም ተከተል ባለቸው ተነፃፃሪ ጠቀሜታ ወይም comparative advantage እና ጂኦግራፊያው ሁኔታ የሚለያዩ ናቸው።

ክቡር ጠቅላይ ሚኒስትራችን ከሀገራቱ መሪዎች ጋር ያደረጉዋቸው ውይይቶች፣ የተመረጡ የመስክ ምልከታዎች እና የተደረጉ የትብብር ማዕቀፎች ብሎም ኢትዮጵያ ለውጭ ባለሃብቶች እየከፈተች ያለው አዳዲስ የኢንቨስትመንትና የገበያ ዕድሎችን የማስተዋወቅ ጉዳይ እነዚህኑ ሁኔታዎች ታሳቢ ያደረጉ ናቸው።

በውይይት የዳበሩት እነዚሁ የትብብር ማዕቀፍ ስልቶችም ሀገራችን ከነደፈቻቻው ፖሊሲዎች እና የእድገት አቅጣጫዎች ጋር እንዲጣጣሙ ጥረት የተደረገባቸው ናቸው።ከዚህ አኳያ ክቡር ጠቅላይ ሚኒስትር ዐብይ አህመድ (ዶ/ር) እና የልዑክ ቡድናቸው በሁለቱም ሀገሮች የነበረቸው ቆይታ ፍሬያማ እና የተሳካ ነበር።


 

ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ (ዶ/ር) በኮሪያ ያደረጉት ጉብኝት ታሪክን ከማስታወስ የጀመረ ነው። ኢትዮጵያ በ1950ዎቹ የኮሪያ ጦርነት በሰላም ማስከበር ተልዕኮ ተሰማርታ ለኮሪያ ሰላም መስዋዕትነት የከፈሉ የቃኘው ሻለቃ ጦር አባላትን በማስታወስ፣ የሁለቱ ሀገራት ህዝቦች ግንኙነት በደም የተሳሰረ መሆኑን ባመላከተ አግባብ በቹንችዮን፣ የኮሪያ ጦርነት የመታሰቢያ ስፍራ የአበባ ጉንጉን አስቀምጠዋል። ይህም ኢትዮጵያ በዓለም የሰላም ማስከበር ታሪክ ቀዳሚ ሚና እንዳላትና ለሰላም ያላት ዋጋ ሁልጊዜም የማይለዋወጥ መሆኑ የተገለፀበት፣ የሁለቱ ሀገራት ግንኙነት ከ60 ዓመት በላይ ያስቆጠረና የሀገራቱ የመጪው ጊዜ ግንኙነት የበለጠ ጠንካራ እና ዘርፈ ብዙ ሆኖ እንደሚቀጥል የተመላከተበት ነው።

ጠቅላይ ሚኒስትር ዶ/ር ዐቢይ፣ በኮሪያ ሪፐብሊክ ከሀገሪቱ መሪ ጋር በነበራቸው ቆይታ ሁለቱን ሀገራት ተጠቃሚ በሚያደርጉ የኢኮኖሚ ትብብር ማዕቀፎች ላይ ስምምነት ተደርሷል። የመግባቢያ ስምምነትም ተፈርሟል። ኢትዮጵያን ለአራት ተከታታይ ዓመታት ተጠቃሚ የሚያደርግ የፋይናንስ ድጋፍም ተገኝቷል። በኮሪያ መንግስት ድጋፍ በአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር እየተከናወነ የሚገኘው የወንዝ ዳርቻ ልማት ይበልጥ በሚጠናከርበት ሁኔታም ላይ ስምምነት ተደርሷል።

የኮሪያ ባለሀብቶች በኢትዮጵያ ባሉ የኢንቨስትመንት ዕድሎች በተለይም በግብርና፣ በማዕድንና በአምራች ኢንደስትሪ ዘርፎች በሚሳተፉበት ሁኔታ ላይ ምክክር ተደርጓል። ከውይይቶቹም ጎን ለጎን ሀገራችን ለጀመረችው ፈጣንና አመርቂ የልማት ስራዎች ልምድ መቅሰም የሚያስችሉ የመስክ ምልከታዎች ተካሂዷል ። የልዑካን ቡድናቸውም የመሪዎቹን ስምምነቶችና ውይይቶች ታሳቢ ያደረጉ እና ይበልጥ የሚያፀኑ ውይይቶችን ከአቻ ተቋማት መሪዎች ጋር አካሂደዋል።


 

በኮሪያ የተሳካ ጉብኝታቸውን አጠናቀው ወደ ሲንጋፖር ያመሩት ክቡር ጠቅላይ ሚኒስትር ዐብይ አሕመድ፣ በሲንጋፖር በነበራቸው ቆይታ ከሀገሪቱ ፕሬዚዳንት እና ጠቅላይ ሚንስትር ጋር በሁለትዮሽ ግንኙነት ጉዳይ ተወያይተዋል። በጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ (ዶ/ር) የተመራው ልዑክም የኢትዮጵያ መሪ ወደ ሲንጋፖር ከተጓዘ ከ68 ዓመታት በኋላ የተጓዘ የመጀመሪያው ልዑክ ሆኗል።

የሲንጋፖርና የኢትዮጵያ ይፋዊ ያልሆነ ግንኙነት የሚጀምረው የሲንጋፖር መስራች አባት የሚባሉት ጠቅላይ ሚኒስትር ሊ ኩዋን ዩ በፈረንጆቹ 1964 ኢትዮጵያን በጎበኙበት ወቅት ነው፤ የጉብኝታቸው ምክንያትም ሲንጋፖር በቅኝ ግዛት ስለነበረች ነጻነቷን ለማግኘት የአፍሪካ ሀገራትን ለማግባባት ነበር። በዚያው ዓመት በርካታ የአፍሪካ ሀገራት ነጻነታቸውን ለመቀዳጀት ጫፍ ላይ የነበሩበት በመሆኑና ተመሳሳይ የጸረ ቅኝ ግዛት ትግል አቋም በመኖሩ ለሲንጋፖር አፍሪካ ተመራጭ አህጉር ነበር። ከዚህ አኳያ ኢትዮጵያ ከኮሪያም ሆነ ከሲንጋፖር ጋር ያላት ታሪካዊ ግንኙነት አሁን ያልጀመረና የጠበቀ ትስስር እንዳለው ያመለክታል።

ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ በሲንጋፖር ከሀገሪቱ መሪዎች ጋር የነበራቸው ውይይት አንዱ ትኩረት አረንጓዴ ልማት ሲሆን በትምህርት፣ በቀልጣፋ የህዝብ አገልግሎት እንዲሁም በከተማ ልማት ስራዎች ዙሪያ ሀሳቦችን ተለዋውጠዋል።

በኢትዮጵያ እና በቀጠናው ስላለው የሰላም ሁኔታ፣ የኢንቨስትመንት አማራጮች እና ዕድሎች እንዲሁም በቴክኖሎጂ፣ በሎጀስቲክ እና ትራንስፖርት፣ በቱሪዝም ዘርፎች ፣ እንዲሁም በቀጣይ የትብብር መስኮች ላይ ሰፋ ያለ ውይይት አካሂደዋል።


 

የሁለትዮሽ ግንኙነትን የሚያጠናክር የስምምነት ማዕቀፍም ተፈርሟል። ሲንጋፖር በአገልግሎት ዘርፍ፣ በቴክኖሎጂ፣ በቱሪዝም እና በሎጂስቲክ ሀብ የላቀ ደረጃ ላይ የደረሰች ሀገር በመሆኗ ኢትዮጵያ ለጀመረችው የአራንጓዴ አሻራ፣ የቱሪዝም መሠረተ ልማት ግንባታ እና የኮሪደር ልማት ሰፊ ልምድ የሚቀሰምባት ናት።

ይህ እንዳለ ሆኖ ጉብኝቱ ሲንጋፖር ተመራጭነቷን በአረንጓዴ ልማት ጭምር እንዴት እያሳካች እንደሆነ ትምህርት የተወሰደበትና ኢትዮጵያ የጀመረችው የአረንጓዴ ልማት ስራዎች በትክክለኛ ደረጃ እየተጓዙ ስለመሆኑ ግንዛቤ የተገኘበት፣ ይህንኑ ታሳቢ ያደረጉም የተመረጡ የመስክ ምልከታዎች የተካሄዱበት ነው።

በሀገሪቱ ቁልፍ ለሆኑና እና ለተመረጡ ባለሀብቶች በኢትዮጵያ ስላለው የኢንቬስትመንት አማራጮች፣ የፖሊሲ ማሻሻያዎችና ተያያዥ ጉዳዮች በልዑኩ ገለጻ ተደርጎላቸዋል። ባለሀብቶቹ ላነሱት ጥያቄዎችም አጥጋቢ ምላሽ ተሰጥቶአቸዋል።

ባለሀብቶቹም በተለይም በቴክኖሎጂ፣ በሎጅስቲክስ እና ደረቅ ወደብ ግንባታ እና አስተዳደር ፣ በግብርና ልማት እና አገልግሎት መስኮች ለመሰማራት ፍላጎት እንዳላቸው ገልፅዋል።

ከዚህ አኳያ ሲታይ ክቡር ጠቅላይ ሚንስትሩ እና የልዑክ ቡድናቸው በሁለቱም ሀገሮች የነበረቸው ቆይታ ፍሬያማ እና የተሳካ፣ የኢትዮጵያ ተፈላጊነትና አስፈላጊነት የታየበት ነበር። በሁለቱም ሀገሮች ለክቡር ጠቅላይ ሚንስትሩ እና ልዑካቸው ወንድማዊ እና ፍቅር የተሞላበት ደማቅ አቀባበል ተደርጓል። በዚህ አጋጣሚ የሁለቱንም ሀገር መንግስት እና ህዝብ ከልብ እናመሰግናለን!!

የመንግስት ኮሙኒኬሽን አገልግሎት ሚኒስትር ለገሰ ቱሉ (ዶ/ር)

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም