ለዘንድሮው የአረንጓዴ አሻራ መርሐ ግብር የመዲናዋን አየር ንብረት ያማከሉ የችግኝ ዝርያዎች በጥናት ተለይተዋል - የአዲስ አበባ የከተማ ውበትና አረንጓዴ ልማት ቢሮ - ኢዜአ አማርኛ
ለዘንድሮው የአረንጓዴ አሻራ መርሐ ግብር የመዲናዋን አየር ንብረት ያማከሉ የችግኝ ዝርያዎች በጥናት ተለይተዋል - የአዲስ አበባ የከተማ ውበትና አረንጓዴ ልማት ቢሮ
አዲስ አበባ፤ ግንቦት 30/2016(ኢዜአ)፦ ለዘንድሮው የአረንጓዴ አሻራ መርሐ ግብር የመዲናዋን አየር ንብረት ያማከሉ የችግኝ ዝርያዎች በጥናት መለየታቸውን የአዲስ አበባ የከተማ ውበትና አረንጓዴ ልማት ቢሮ ገለፀ።
በጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ (ዶ/ር) ሐሳብ አመንጪነት ከአምስት ዓመታት በፊት የተጀመረው የአረንጓዴ አሻራ መርሃ ግብር ዘንድሮም ለስድስተኛ ጊዜ ይከናወናል።
ለተከታታይ ዓመታት የተተገበረው መርሐ ግብሩ ማህበረሰቡ ለቀጣይ ትውልድ የራሱን አረንጓዴ አሻራ ያሳረፉ ሲሆን፤ ይህም የደን ሽፋንን በመጨመር ለአካባቢ መራቆት ተግባራዊ ምላሽ ሰጥቷል፡፡
የአዲስ አበባ የከተማ ውበትና አረንጓዴ ልማት ቢሮ ኃላፊ ይመኙሻል ታደሰ እንደሚሉት በመርሐ ግብሩ የመዲናዋን የደን ሽፋን ከ2 ነጥብ 8 በመቶ ወደ 15 በመቶ ማሳደግ ተችሏል።
መርሐ ግብሩ በአየር ንብረት ለውጥ መከላከል ረገድ የራሱ አወንታዊ ሚና መጫወቱን ገልጸው፤ ችግኝ የመትከል ባህል እና የፅድቀት መጠን በየዓመቱ እያደገ መጥቷል ይላሉ።
ለአብነትም በ2014/2015 ዓ.ም 84 በመቶ የነበረው የችግኞች የጽድቀት መጠን 2015/16 ዓ.ም 89 በመቶ መድረሱን ጠቅሰው፤ በየዓመቱ ልምድና ተሞክሮዎችን በመቀመር ስኬታማ ስራዎች ማከናወን መቻሉን ተናገረዋል።
መዲናዋ የተለያዩ የአየር ንብረት ያላቸውን አካባቢዎች እንደምታቅፍ ጠቅሰው፤ ከዘንድሮው የአረንጓዴ አሻራ መርሐ ግብር ትግበራ የመዲናዋን የአየር ንብረት ያማከለ ይሆናል ብለዋል።
ለዚህ ደግሞ ከአጋር አካላት ጋር በመተባበር ለመዲናዋ የአየር ንብረት የሚስማሙ ችግኝ ዝርያዎችን ለመትከል በጥናት መለየቱን ነው የተናገሩት።