ቀጥታ፡

የኢትዮጵያ አየር መንገድ አፍሪካን በማስተሳሰር ለአህጉሪቷ ነጻ የንግድ ቀጠና መሳለጥ ሚናውን አጠናክሮ ይቀጥላል - አቶ መስፍን ጣሰው

አዲስ አበባ፤ ግንቦት 30/2016(ኢዜአ)፦  የኢትዮጵያ አየር መንገድ  አፍሪካን በአየር ትራንስፖርት በማስተሳሰር ለአህጉሪቷ ነጻ የንግድ ቀጠና መሳለጥ ሚናውን አጠናክሮ እንደሚቀጥል የኢትዮጵያ አየር መንገድ ግሩፕ ዋና ስራ አስፈጻሚ መስፍን ጣሰው ገለጹ። 

የአፍሪካ ህብረት እንደ አውሮፓዊያን አቆጣጠር መጋቢት 2018 በሩዋንዳ መዲና ኪጋሊ ባካሄደው የመሪዎች ጉባኤ የተሳተፉ 44 የአፍሪካ አገሮች የአህጉሪቷን ነጻ የንግድ ቀጣና እውን ለማድረግ መፈራረማቸው ይታወሳል፡፡

ስምምነቱም እንደ አውሮፓዊያን አቆጣጠር ጥር 1 ቀን 2021 ጀምሮ ተግባራዊ የተደረገ  ሲሆን፤ ኢትዮጵያ በአየር መንገዷ በኩል በአፍሪካ ነጻ የንግድ ቀጠና የሚጓጓዘውን የመጀመሪያ ጭነት ከኤስዋቲኒ ወደ አዲስ አበባ በማምጣት እንዲጀመር አድርጋለች፡፡

ስምምነቱ ሙሉ ለሙሉ ተግባራዊ ሲደረግም በ2034 በአፍሪካ አገሮች መካከል ያለውን የንግድ ልውውጥ በ60 በመቶ በማሳደግ በመካከላቸው ያለውን የሸቀጦች የንግድ ታሪፍ በ90 በመቶ እንደሚያስቀርም ነው የሚገለጸው፡፡

የ3 ነጥብ 4 ትሪሊዮን ዶላር ዓመታዊ ምርት ድረሻ እንደሚኖረውም እንዲሁ፡፡

ኢትዮጵያ አየር መንገድ ግሩፕ ዋና ስራ አስፈጻሚ መስፍን ጣሰው፤ ለአፍሪካ አህጉር ነጻ የንግድ ቀጠና ውጤታማነት የአየር ትራንስፖርት ትስስር ትልቁን ድርሻ እንደሚይዝ ለኢዜአ ተናግረዋል።

በአህጉሪቷ መካከል ያለውን የሰዎች እንዲሁም የሸቀጦች ማጓጓዝን በማሳለጥ ተመጋጋቢ የሆነ የኢኮኖሚ ትስስር ለመፍጠር እንደሚያግዝ ጠቅሰው፤ ለዚህ ደግሞ የአየር ትራንስፖርት ትስስር ሚናው ከፍተኛ ስለመሆኑ አብራርተዋል፡፡

በዚህም የኢትዮጵያ አየር መንገድ አህጉሪቷን በማስተሳሰር የአፍሪካ መሪዎች የወጠኑትን አህጉራዊ ነጻ  የንግድ ቀጠና ውጤታማነት ሚናውን አጠናክሮ ቀጥሏል ነው ያሉት፡፡

አየር መንገዱ በአፍሪካ ያሉትን መዳረሻዎች እያሳደገ ሲሆን በአሁኑ ወቅት  64 የአፍሪካ ከተሞች ላይ እንደሚበር ገልጸዋል።

ይህም አየር መንገዱ አብዛኛውን የአፍሪካን ሀገራት በአየር ትራንስፖርት የማስተሳሰር ተግባሩን እያፋጠነ መሆኑን ማሳያ ነው ብለዋል።

በጥቂት ጊዜ ውስጥም አየር መንገዱ የቀሩትን ጥቂት የአፍሪካ ሀገራት በአየር ትራንስፖርት የማስተሳሰር ስራ ይሰራል ነው ያሉት።

የኢትዮጵያ አየር መንገድ ባሉት 147 በላይ አውሮፕላኖች 136 ዓለም አቀፍና 22 የአገር ውስጥ መዳረሻዎችን እየሸፈነ ይገኛል።

 

 

 

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም